የፌዴራልና የክልል መንግሥታት የሚሰበስቡት ኃብትን በፍትሃዊነት በማከፋፈል አበረታች ሥራ ተሰርቷል - ኢዜአ አማርኛ
የፌዴራልና የክልል መንግሥታት የሚሰበስቡት ኃብትን በፍትሃዊነት በማከፋፈል አበረታች ሥራ ተሰርቷል
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 22/2016(ኢዜአ)፦ባለፉት ዓመታት የፌዴራልና የክልል መንግሥታት የሚሰበስቡት ኃብትን በፍትሃዊነት በማከፋፈል አበረታች ሥራ መሠራቱን የፌዴሬሽን ምክር ቤት ገለጸ።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት "የፊስካል ፌዴራሊዝም መሠረታዊ ጉዳዮችና የኢትዮጵያን ተጨባጭ ሁኔታ" በሚዳስስ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት ሥልጠና ሰጥቷል።
በሥልጠናው የምክር ቤቱ ምክትል አፈ-ጉባዔ ዛህራ ሁመድ፣ የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮችና አፈ-ጉባዔዎች እንዲሁም የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት ተሳትፈዋል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር በዚሁ ጊዜ፤ የፌዴራሊዝም ሥርዓት የመንግሥት አወቃቀር የሀገርን ዘላቂ ሰላም፣ የሕዝብ እኩልነት፣ አብሮነትና የጋራ የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ጉልህ ፋይዳ አለው ብለዋል።
ፍትሃዊ የኃብት ክፍፍል፣ ውጤታማ የፊስካል ሽግግርና የክልሎችን የተመጣጠነ ዕድገት ማሳለጥ ለጠንካራ ሕብረ-ብሔራዊ የፌዴራል ሥርዓት ግንባታ ጽኑ መሠረቶች መሆናቸውን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ የበይነ-መንግሥታት የፊሲካል ሽግግር ሥርዓትም በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 62 መሠረት ለፌዴሬሽን ምክር ቤት በተሰጠው ሥልጣን ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤትም ጥቅል የድጎማ በጀትንና ከመንግሥትም ሆነ ዓለም አቀፍ አጋሮች ለተለየ ዓላማ የሚደረግን፣ የሚደለደልን ኃብት በፍትሃዊነት ለክልሎች በማከፋፈል የክትትል ሥራ እንደሚሰራ ገልፀዋል።
የክልሎች የተመጣጠነ ዕድገት በማረጋገጥ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን የሚረዱ ቀመሮችን፣ የሕግ ማዕቀፍና አሠራር በመዘርጋት ተግባራዊ እንዲሆኑ እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል።
የፌዴራልና የክልል መንግሥታት በጋራ የሚሰበስቡት ኃብት በትክክል ግልጽነትና ፍትሃዊነትን በተላበሰ መልኩ ለክልሎች በማከፋፈል ከፍተኛ ለውጥ መምጣቱን ተናግረዋል።
በምክር ቤቱ የድጎማ በጀትና የጋራ ገቢዎች ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ጸሐፊ ኃይሉ ኢፋ፤ የበይነ-መንግሥታት የፊሲካል ሽግግር የገቢና ወጪ የአሠራር ሥርዓቶችን ማስገንዘብ የሥልጠናው ዓላማ ነው ብለዋል።
በፍትሃዊና ውጤታማነት መርህ የፌዴራል ፊሲካል በጀት ድልድል በማድረግ የፌዴራል መንግሥት በሁሉም ክልሎች ሰፋፊ የመሠረተ-ልማት አውታሮችን እየገነባ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
የክልል መንግሥታትን ጥያቄና መረጃን መሠረት በማድረግ ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ የጋራ ገቢ ቀመርን በማሻሻል ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገብ እንደተቻለ ተናግረዋል።
የጋራ ገቢ ቀመር መሻሻሉም በ2012 ዓ.ም የክልሎች ድርሻ ከነበረበት የ4 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር በየዓመቱ ዕድገትን እያስመዘገበ አሁን ላይ በ11 ወራት ብቻ 56 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር ደርሷል ብለዋል።
የምክር ቤቱ የፊሲካል ጉዳዮችና የክልሎች የተመጣጠነ ዕድገት ዳይሬክተር ዋቅቶሌ ዳዲ(ዶ/ር) ባቀረቡት የፊስካል ፌዴራሊዝም መሠረታዊ ጉዳዮችና የኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ የመነሻ ጽሑፍ አስተያየትና ጥያቄ ቀርቦ ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶበታል።