ቀጥታ፡

በበጀት ዓመቱ በኢንቨስትመንት የተሰማሩ የዳያስፖራ አባላት 3 ሺህ ለሚጠጉ ዜጎች የሥራ ዕድል ፈጥረዋል 

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 22/2016(ኢዜአ)፦በበጀት ዓመቱ በኢንቨስትመንት የተሰማሩ የዳያስፖራ አባላት 3 ሺህ ለሚጠጉ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን  የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ገለጸ።  
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ከፌዴራል ተቋማት፣ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የዳያስፖራ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤቶች ጋር በ2016 ዕቅድ አፈጻጸም ላይ ተወያይቷል። 


 

የአገልግሎቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር በላይነህ አቅናው በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ ዳያስፖራዎች አገራዊ ፕሮጀክቶችን በመደገፍ፣ ገንዘብ ወደ ሀገር በመላክና በበጎ አድራጎት ሥራዎች ያላቸው ተሳትፎ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ተናግረዋል።  

ይህንንም ተከትሎ በ2016 በጀት ዓመት በኢንቨስትመንትና ከውጭ የተላከን ገንዘብ (ሪሚታንስን) ሳይጨምር ለሀገራዊ ፕሮጀክቶችና ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከቦንድ ሽያጭ እና ከልዩ ልዩ ሥራዎች 750 ሺህ ዶላር ማስገኘት ተችሏል ብለዋል። 

ለገበታ ለሀገርና ለጽዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ 1 ነጥብ 6 ሚሊየን ዶላር አስተዋጽዖ ማድረጋቸውን ጠቁመው፤ ለልዩ ልዩ ድጋፎችና በጎ አድራጎት ሥራዎች 18 ነጥብ 6 ሚሊየን ዶላር መሰብሰብ መቻሉን አመላክተዋል።

በአጠቃላይ በዚህ በጀት ዓመት ከዳያስፖራው ማኅበረሰብ በዓይነት፣ በገንዘብና በጥሬ ማሰባሰብ የተቻለው 20 ሚሊየን ዶላር መሆኑን ጠቁመዋል።

ዳያስፖራው ለአገራዊ ልማት ከሚያደርገው ድጋፍ በተጨማሪ መንግሥት በኢንቨስትመንት እንዲሰማራ በማድረግ ውጤቶች እየተመዘገቡ መሆኑን አንስተዋል።  

በዚህም በበጀት ዓመቱ 72 ነጥብ 48 ቢሊየን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ የዳያስፖራ ኢንቨስትመንቶች ፈቃድ መሰጠቱን ተናግረዋል።

ከእነዚህም ውስጥ ለ273 ኢንቨስትመንቶች መሬት እንደተመቻቸላቸው እና 55 ኢንቨስትመንቶች ወደ ሥራ መግባታቸውን ተናግረዋል።

ወደ ሥራ የገቡ ኢንቨስትመንቶች እስካሁን ለ3 ሺህ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን አመላክተዋል። 

 

 
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም