ስፖርት የአገር መከላከያ ሠራዊት የተሟላ ቁመና እንዲይዝ በማድረግ ግዳጁን በብቃት እንዲወጣ የሚያስችል ነው - ኢዜአ አማርኛ
ስፖርት የአገር መከላከያ ሠራዊት የተሟላ ቁመና እንዲይዝ በማድረግ ግዳጁን በብቃት እንዲወጣ የሚያስችል ነው
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 22/2016(ኢዜአ)፦ስፖርት የአገር መከላከያ ሠራዊት የተሟላ ቁመናን እንዲይዝ በማድረግ ግዳጁን በብቃት እንዲወጣ የሚያስችል ሁነኛ መሳሪያ መሆኑን የመከላከያ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሐመድ ገለጹ።
ስፖርትና ሠራዊት ሊነጣጠሉ የማይችሉ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው ብለዋል።
የመከላከያ ሚኒስቴር የመቻል ስፖርት ክለብ 80ኛ የምስረታ በዓልን አስመልክቶ ያዘጋጀው የፓናል ውይይት ዛሬ በመከላከያ ዋና መምሪያ ተካሂዷል።
የመከላከያ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሐመድ፤ በአገራዊ ለውጡ ተጨባጭ ውጤት ከታየባቸው ተቋማት አንዱ የአገር መከላከያ ሠራዊት መሆኑን ገልፀዋል።
የሪፎርሙ አካል በሆነው የሠራዊት ግንባታ የአስተሳሰብና የተግባር ለውጥ መምጣቱንና በሥልጠናና ሥርፀት የሠራዊቱን ሞራልና አቅም መገንባት መቻሉን አመልክተዋል።
ወታደር በአካል፣ በአዕምሮና ሥነ-ልቦና ዝግጁ መሆን እንደሚገባው ለዚህም ስፖርት ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት ተናግረዋል።
ስፖርት ሠራዊቱ የተሟላ ቁመና እንዲኖረው በማድረግ እንዲሁም ግዳጁን በብቃት እንዲወጣ ሁነኛ መሳሪያ ነው ብለዋል።
ከዚህም አንጻር ስፖርትና ሠራዊት ሊነጣጠሉ የማይችሉ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች መሆናቸውን ነው ሚኒስትሯ የተናገሩት።
ይህም ስፖርት የሠራዊቱን ገጽታ ለመገንባትና ከሕዝቡ ጋር መልካም ግንኙነት ለመፍጠር እንደሚያስችለው ገልፀዋል።
መቻል ስፖርት ክለብ 80ኛ የምስረታ በዓሉን ከሰኔ 1 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ መርኃ-ግብሮች እያከበረ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
መቻል በ80 ዓመት ታሪኩ በአገር ደረጃ እንዲሁም በአህጉራዊና ዓለም አቀፍ የስፖርት መድረኮች በርካታ ስፖርተኞችን በማሳተፍና ውጤታማ በመሆን የበኩሉን ያበረከተ የስፖርት ክለብ እንደሆነ ተናግረዋል።
የመቻልን የቀደመ ገናናነት ለመመለስ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝም ገልፀዋል።
የአገር መከላከያ ሠራዊት የሥነ-ልቦና ግንባታ ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጄኔራል እንዳልካቸው ወልደኪዳን፤ የመቻል ስፖርት ክለብ ራዕይ ራሱን ማጠናከር ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያ ስፖርት እድገት ማደግ የበኩሉን ድርሻ መወጣት መሆኑን አመልክተዋል።
ሁሉም ኢትዮጵያዊ ለመቻል መጠናከርና ስኬት የበኩሉን አስተዋጽዖ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስፖርት ሳይንስ ትምህርት ክፍል ኃላፊና መምህር ዘሩ በቀለ (ዶ/ር) የመቻል ስፖርት ክለብ ዘላቂነት ያለውና የማይነጥፍ የፋይናንስ ኃብት ማሰባሰቢያ መንገዶች ሊኖሩት ይገባል ብለዋል።
ለዚህም የክለቡ አርማ(ሎጎ) ላይ የማስተዋወቅ ሥራ መሥራት፣ ከድርጅቶችና ባለኃብቶች ጋር ትስስር መፍጠርና የስፖርት ምርቶቹን የሚሸጥባቸውን ቋሚ ሁነቶች በማዘጋጀት የገንዘብ አቅሙን ማጠናከር እንደሚችል ገልፀዋል።
የመቻል ስፖርት ክለብ ተጨዋችና አሰልጣኝ የነበረው ዮሐንስ ሳህሌ፤ የስፖርት እድገትን ያለ ፋይናንስ አቅም እውን ማድረግ እንደማይቻል ጠቅሰው፤ መቻል የፋይናንስ አቅሙን ማጎልበት ላይ በትኩረት መሥራት እንዳለበት ገልጿል።
መቻል በተለያዩ የስፖርት ዘርፎች ላይ ያለውን አቅም በማጠናከር ተፎካካሪ ስፖርተኞችን ማፍራት ላይ አበክሮ መሥራት አለበት ብሏል።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የጽህፈት ቤት ኃላፊ ባህሩ ጥላሁን፤ መቻል በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ ያሳረፈውን ትልቅ አሻራ ይዞ ለመቀጠል ስታዲየምን ጨምሮ የራሱን የስፖርት መሠረተ-ልማቶች ማሟላት እንዳለበት ገልፀዋል።
የስፖርት ክለቡ ፕሮፌሽናል ደረጃውን የጠበቀ የአደረጃጀት መዋቅር እንዲኖረው መሥራት እንደሚያስፈልግም አመልክተዋል።
በፓናል ውይይቱ የመቻል ስፖርት ክለብ ከምሥረታው አንስቶ እስካሁን ያለፈባቸው ጊዜያትና ቀጣይ ክለቡን ይበልጥ ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ የተዘጋጁ የመነሻ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።
በውይይቱ ላይ የክለቡ አንጋፋና አሁን ላይ እየተወዳደሩ ያሉ ስፖርተኞችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
የመከላከያ ሚኒስቴር የመቻል ስፖርት ክለብን 80ኛ የምሥረታ በዓል "መቻል ለኢትዮጵያ" በሚል መሪ ኃሳብ እያከበረ መሆኑ ይታወቃል።