ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ክልል ክለቦች ሻምፒዮና በድሬዳዋ ተጀመረ

ድሬዳዋ፤ ሰኔ 22/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የክልል ክለቦች የእግርኳስ ውድድር ሻምፒዮና ዛሬ  ከሰዓት  በድሬዳዋ  ስታዲየም ተጀመረ። 

በመክፈቻው ስነ-ስርዓት ተገኝተው  ከተጫዋቾች ጋር በመተዋወቅ ውድድሩን ያስጀመሩት የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ሀርቢ ቡህ፣ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ እንዲሁም የድሬዳዋ ወጣቶችና ስፖርት ኮሚሽነር ካሊድ መሐመድ ናቸው።


 

እስከ ሐምሌ 16 ቀን የሚቆየው የክልል ክለቦች ሻምፒዮና ውድድር ዓላማ አራት  ለግማሽ ፍፃሜ የሚደርሱ ክለቦችን በመለየት  በሚቀጥለው ዓመት በሚካሄደው የኢትዮጵያ አንደኛ ሊግ ለማሳደግ እንደሆነ ተገልጿል።

የውድድር ስነ-ስርዓት ኮሚቴ አባል  አቶ ዘገየ ቦጋለ ለኢዜአ እንደተናገሩት ፤ በኢትዮጵያ ክልል ሻምፒዮና የተሳተፉት ክለቦች በየክልላቸውና ከተማቸው በተካሄዱ ውድድሮች  አሸናፊ ሆነው የተመረጡ ናቸው።


 

ውድድሩ ለእነዚህ ክልቦች ቀጣይ  ጉዞ  ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር እና   አራት ለግማሽ ፍፃሜ የሚደርሱ ክለቦችን በ2017 ዓ.ም ወደ ኢትዮ አንደኛ ሊግ ለማሳደግ የሚያስችል ይሆናል ብለዋል።

በተጨማሪም ምርጥ ተተኪ ስፖርተኞችን ለመመልመልም እንደሚያስችልም ተናግረዋል።

ዛሬ ከሰዓት   በተጀመረው የመክፈቻ ውድድር ጊንጪና  ድሬደዋ መስቀለኛ ሶስት አቻ በመለያየት ነጥብ ተጋርተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም