አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ከተማዋን የሚመጥን የሚዲያ ተቋም ለመሆን ለሚያከናውናቸው ተግባራት አስፈላጊው ድጋፍ ይደረጋል - ኢዜአ አማርኛ
አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ከተማዋን የሚመጥን የሚዲያ ተቋም ለመሆን ለሚያከናውናቸው ተግባራት አስፈላጊው ድጋፍ ይደረጋል
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 22/2016(ኢዜአ)፦አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ከተማዋን የሚመጥን የሚዲያ ተቋም ለመሆን ለሚያከናውናቸው ተግባራት ከተማ አስተዳደሩ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ አዲሱን የቋንቋዎች ቻናል (AMN PLUS)፣ አዲስ ብራንድ እና “አዲስ ታለንት ሾው” የተሰኘ የኪነ-ጥበብ ውድድር ፕሮግራምን በይፋ አስጀምረዋል።
በዛሬው ዕለት በይፋ የሚጀምረው አዲሱ ቻናል (AMN PLUS) ተጨማሪ ቋንቋዎችን ለተመልካች ተደራሽ ለማድረግ እንደሚያስችል ተመላክቷል።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ አዲሱ ቻናል አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዘመኑን በሚመጥን ቴክኖሎጂ፣ የሰው ኃይል፣ ሥነ-ምግባርና በአገልጋይነት መንፈስ ይበልጥ የሚታይበት ነው።
ተቋሙ የብዙኃን ድምፅ መሆኑን በተግባር እያሳየ፤ ተወዳዳሪና ከተማዋን የሚመጥን ሚዲያ ለመሆንም ተከታታይነት ያለው ያልተቋረጠ ሥራ መሥራት እንደሚገባም ገልፀዋል።
ይህም ብቻ ሳይሆን ተቋሙ የከተማዋን ፈጣን እድገት የሚመጥን ሥራ መሥራት እንዳለበት ገልጸው፤ ለዚህም ከተማ አስተዳደሩ አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።
አዲስ አበባ ከቆሻሻ እየፀዳች ጎስቋላ ገጽታዎቿ እየተቀየሩ መሆኑን ገልጸው፤ እነዚህ ሥራዎች የበለጠ ውጤታማ እንዲሆኑ በትብብር መሥራት እንደሚገባም ጠቅሰዋል።
እነዚህ ጥረቶች የበለጠ የሚፋጠኑት ሕዝቡ ትክክለኛ መረጃ ሲያገኝ በመሆኑ፤ ለዚህም በሚሰራው ሥራ ላይ ለኅብረተሰቡ ግንዛቤ መፍጠር እንደሚገባ ጠቁመዋል።
የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት በዚህ ረገድ የሚጠበቅባቸውን ሚና መወጣት እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር መሀመድ እድሪስ፤ አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ከተማዋን የሚመጥን የሚዲያ ተቋም ለመሆን እየሄደበት ያለውን ርቀት የሚደነቅ ነው ብለዋል።
እንዲያም ሆኖ ተቋሙ ከከተማዋ እድገት ጋር እኩል ሊራመድ እንደሚገባ ገልጸው፤ በተለይም ተቋሙ ስለ አዲስ አበባ መረጃ የሚገኝበት ቋት ሊሆን እንደሚገባም ነው ያመላከቱት።
የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ካሳሁን ጎንፋ፤ ተቋሙ የከተማዋ ድምፅና የብዝኃነት አንደበት ሆኖ እያገለገለ ይገኛል ብለዋል።
አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ከከተማዋ እድገት ጋር አብሮ ከፍ እያለ የመጣ ተቋም መሆኑንም ገልፀዋል።
ተቋሙ በሬዲዮ፣ በሕትመት እንዲሁም በዲጂታል አማራጮች መረጃዎችን ተደራሽ እያደረገ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
በሰባት ቋንቋዎች መረጃዎችን ለአድማጭ ተመልካች እያቀረበ መሆኑን ገልጸው፤ በተጨማሪ ሦስት ቋንቋዎች ለመጨመር ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
ተቋሙ በሁሉም የሚዲያ ዘርፎች ተወዳዳሪ፣ ተመራጭና ተደራሽ የሚያደርገውን አቀራረብና ይዘት ወደ አድማጭ ተመልካቾች ለማድረስ እየሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
በመዝናኛው ዘርፍ ወጣቶች ተሰጧቸውን የሚያሳዩበት “አዲስ ታለንት ሾው” የተሰኘ የኪነ-ጥበብ ውድድር በዛሬው ዕለት እንደሚጀምር ጠቁመዋል።
ከተማ አስተዳደሩ ተቋሙ እያከናወነ ላለው ሥራ እያደረገ ላለው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።
ኤ ኤም ኤን ቋንቋዎች (AMN plus) በኢቲዮ ሳት ፍሪኩዌንሲ - 10985 MHz ፖላራይዜሽን - horizontal ሲምቦል ሬት - 45000 FEC - 5/6 ላይ ይገኛል።
አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ በ2023 ተመራጭ ሜትሮፖሊታን ሚዲያ የመሆን ራዕይን ሰንቆ እየሰራ ነው።