የአማራ ክልል የሰላም ካውንስል ያቀረበው የሰላም ጥሪ - ኢዜአ አማርኛ
የአማራ ክልል የሰላም ካውንስል ያቀረበው የሰላም ጥሪ
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 22/2016(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል የተከሰተው ግጭት እንዲፈታ ከህዝብ ተውጣጥቶ የተቋቋመው የሰላም ካውንስል ጥሪ አቀረበ።
ከአማራ ክልል የሰላም ካውንስል የተሰጠ መግለጫ ፦
ሰላም ለሁሉም ሁሉም ለሰላም በሚል በአማራ ክልል ለተፈጠረው ችግር የመፍትሔ ሃሳብ ያመጣሉ ተበለው ከተመረጡ የማህበረተሰብ ከፍሎች ጋር ከሰኔ 17/2016 ዓ.ም እስከ 18/2016ዓ.ም በተደረገው የባህር ዳር ጉባኤ ሁለት ቀን ከመከረ በሗላ በመጨረሻም ያለ ቅድመ ሁኔታ በየትኛውም ደረጃ በየትኛውም ቦታ በየትኛውም አደራዳሪ ሁለቱ ተፋላሚ ሃይሎች ማለትም የመንግስት ሃይሎች እና በጫካ የሚገኙ የፋኖ ወንድሞቻችን ቢያንስ ዘላቂ ተኩስ ለማቆም ንግግርና ድርድር እንዲያደርጉ ጉባኤው መወሰኑና ለዚህ ሂደትም 15 አባላት ያሉት አመቻች የሰላም ካውንስል መርጧል። በመሆኑም የተመረጠው የሰላም ካውንስል ሲወያይ ከሰነበተ በሗላ በዛሬው እለት ሰኔ 22/2016ዓ.ም በሚከተለው መልኩ መግለጫ አውጥቷል።
የአማራ ከልል ህዝብ ከሌሎች የኢትዮጵያ ወንድሞቹ ጋር በመሆን ለኢትዮጵያ ሃገረ መንግሥት ግንባታ ያበረከተው ሚና ከፍተኛ ነው። በመሆኑም ኢትዮጵያን ብቻውን ጠፍጥፎ የሰራት ይመስል አንዳንድ የሀገሩ ልጆች የቀኝ ገዥዎች ሃሳብ በመቀበል የጨቋኝና ተጨቋኝ ትርከት በመፍጠር በተነዛው የሃሰት ፕሮፖጋንዳ ክልሉ አሁን ላለበት ደረጃ አድርሶታል ብለው የሚናገሩ ብዙዎች ናቸው። እርግጥ መልኩ መቀየር ካልሆነ በስተቀር እርስበርስ መዋጋት መፍትሄ ያላመጣ ፣በድህነት ወደኋላ እንድንቀር ያደረገን ፣በሺ አመታት የኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የነበረና ያለ ልንሻገረው ያልቻልን በሗላ ቀርነታችን መገለጫ እንጂ አሁን አዲስ ተፈጥሮ የሚያስደንቀን አይደለም። ምን አልባት ሊያስደንቀን የሚችለው ከታሪካችን መማር አቅቶን ለዛውም በ21ኛው ክ/ዘመን ወደ ጋርዮሽ ዘመን በሚመለስ አይነት አስቀያሚ የእርስበርስ ጦርነት እያስኬድን መገኘታችን ነው። ከሺ ዓመታት በላይ ታሪክ ያለው ሃገር ይዘን መደማመጥ፣መነጋገርና ወደ ጦርነት ሊወስዱ የሚችሉ ቸግሮቻችን በድርድር መፍታት አቅቶን በሴራ ፖለቲካ፣ በሗላ ቀር አመለካከት ወንድም ወንድሙን እያጠፋ ዛሬ ላይ ደርሰናል። ኢትዮጵያዊያን ብዙ የሚያኮራ አድዋን የመሰለ ታሪከ ያለን ቢሆንም እስከ 21ኛው ከ/ዘመን ይዘነው የዘለቀው የእርስበርስ ግጭት ግን የታሪካችን ስብራት፣መሻገር ያቃተን ሁነት መሆኑ ሁላችንም የኢትዮጵያ ዜጎች ሊቆጨን፣ሊከነከንና የመፍትሔ ሃሳብ እንቅልፍ አጥተን ልናስብ ይገባል። እርግጥ አንዳንድ ምሁራን ጦርነት የሀገረ መንግስት ግንባታ አንዱ አካል አድርገው ቢወስዱትም እኛ ኢትዮጵያዊያን ግን ካለን ስሪትና ከመጣንበት መንገድ አንጻር ስን ቃኝ በጦርነት እንጨራረሳለን እንጂ አንሸናነፍም።በአሁኑ ሰዓት የአማራ ህዝብ በዚህ ዘመን ሊፈጠር የማይገባው ግጭት ተፈጥሮ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ምስቅልቅል አጋጥሞት ይገኛል። አማራ ክልል ተከስቶ ያለው ግጭት አጠቃላይ ሃገራችን ለጉዳትና ወደ ባሰ ድህነት አረንቋ እየወሰዳት መሆኑ ግልጽ ነው ለዚህ ግጭት መነሻ ምክንያት
የአማራ ህዝብ ለዘመናት ሲጠይቃቸው የነበሩ ጥያቄዎች በሰለጠነ ንግግርና ድርድር አለመፈታታቸው ወይም የሚፈቱበት ሂደት ግልጽ ፍኖተ ካርታ አለመቀመጡ እንደሆነ ብዙዎች ይስማማሉ : ዋና ዋናዎቹ የአማራ ከልል ህዝብ ጥያቄዎች ተብለው የተለዩት
1. የተዛባ ትርክትን ማረቅና ማስተካከል
2. የህገመንግስት መሻሻልን
3. የወሰንና የማንነት ጉዳይ
4. ፍትሃዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትና የውክልና ጉዳይ
5. በሌሎች ከልሎች የሚኖሩ የአማራ ህዝብ ጉዳይ
በተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች ንጹሃን የአማራ ተወላጆች ለማደርሰባቸው ግድያና መፈናቀል ተጠያቂነት ያለመስፈን ጉዳይ ወዘተ የሚሉ ሆነው ለበርካታ አመታት ትግል ሲደረግባቸው ቆይቷል ።እነዚህ ጥያቄዎች በሃገሪቱ ጥላ ስር በቅንነት በንግግርና በድርድር ሊፈቱ የሚገባቸው እንጂ የኢትዮጵያ ሉአላዊነት የሚፈታተኑ ጥያቄዎች ይመስል ወደ ጦርነት የሚያስገቡ አልነበረም።በተለይ በ2008 በኢትዮጵያ አቆጣጠር የተቀሰቀሰውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ በ2010 በነበረው ለውጥ “የአማራ ህዝብ ጥያቄዎች ሊመልሱ ይችላሉ የሚል ትልቅ ተስፋ ተደርጎ የነበረ ቢሆንም ለጥያቄዎቹ በቂ ትኩረት ሳይሰጣቸው ቀጥሏል።አሁንም የህዝቡ መሰረታዊ ጥያቄዎች ምን ላይ እንዳሉ ምን አይነት የመፍቻ መንገድ እንደተዘጋጀላቸው በተግባር የታየ ግልጽ ነገር የለም ብሎ ያመነው ህዝቡ ጥያቄዎች እንዲመለሱለት በሰላማዊ መንገድ ማለትም በህዝባዊ ሰልፍና ስብሰባ እንዲሁም በኮሚቴዎችና የሃገር ሽማግሌዎች አማካኝነት በተደጋጋሚ ሲጠይቅ ቆይቷል። የክልሉ መንግስትም በህዝቡ ዘንድ ያለው ቅቡልነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ ሂዷል።በተጨማሪም ከችግሩ የሚያወጣው ስትራቴጂካልና ታክቲካል መሪ እያጣ እንዲሁም የተደራጀ የፖለቲካ ግንዛቤ ያለው ማህበረሰብ የሚፈጥርለት ምሁር የመከነበት እስኪመስል ድረስ ደርሷል።በአለፉት አመታት የኢኮኖሚና የማህበራዊ መገለልን የሚቀርፍ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ድጋፍ ይደረጋል ተብሎ ሲጠበቅ ከልሉ በተለያዩ ወቅታዊ አጀንዳዎች በመወጠርና የደህንነት ስጋት ውስጥ እንዲወድቅ በማድረግ ለከፋ የኢኮኖሚ ማሽቆልቆል ተጋልጦ ይገኛል።በተለይ በቅርቡ የፌደራል መንግስት ከህወሃት ጋር በነበረው ጦርነት ለማስቆም ያደረገው የፕሪቶሪያው ስምምነት በአግባቡ ሳይተገበርና የአማራ ህዝብ የህልውና ስጋት ዋስትና ሳይበጅለት የክልሉ ልዩ ሃይል መፍረስና በጦርነት ተሳትፎ የነበራቸው ታጣቂዎች ለህዝቡ በቂ ግልጸኝነት ሳይፈጠር በክልሉ መንግስት የተወሰዱ እርምጃዎች በህዝቡ ላይ ጥርጣሬና ስጋት ፈጥረውበታል።በዚህ ምክንያት የክልሉ የጽጥታ ችግር አየተባባሰ የመጣ ሲሆን ከሀምሌ ወር መጨረሻ 2015 ጀምሮ በከልሉ በነፍጥ የታገዘ ግጭት የተጀመረ ሲሆን ጉዳዩ በመደበኛ የህግ ማስከበር ስርአት ለመቆጣጠር አስቸግሯል በሚል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅ አንድ አመት ለተቃረበ ጊዜ የተደረገው ጦርነት ህዝቡ መከራና ምስቅልቅል ሂወት ውስጥ ገብቶ ይገኛል።በአሁኑ ጊዜ በርካታ የከልሉ አካባቢዎች በመንግስትና የአማራ ህዝብ ጥያቄ ለማስመለስ ጭካ ገባን ባሉ ፋኖዎች መካከል በሚካሄድ በትጥቅ የታግዘ ግጭት ወይም ጦርነት ሳቢያ ብዙ የህዝብ ሃብት ከ12 - 13 ቢሊዮን የሚገመት ንብረት ወድሟል፤ንጽሃን ተገድለዋል ፤ከ3.6 ሚሊዮን በላይ ህጻናት ከትምህርት ገበታ ዉጭ ሆነዋል ፤የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ከፉኛ ተጎድቷል ፤የግልና የመንግስት ተቋማት ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ ባለመቻላቸው ምክንያት የአገልግሎት አሰጣጥ ከፉኛ ተዛብቷል።ነፍሰጡር እናቶች በአግባቡ የአምቡላንስና የወላድ አገልግሎት አያገኙም፤እናቶችና ህጻናት ከጦርነት ተሳትፎ ዉጭ የሆኑ የክልሉ ዜጎች ለከፋ የስነ ልቦና ጫና ተዳርገዋል፤እገታ ተስፋፍቷል፣ዜጎች ያለከልካይ በጠራራ ጸሃይ ይዘረፋሉ፤ይገደላሉ፤ ታላላቅ ፕሮጀከቶች ተስተጓጉለዋል፤ህዝቡ ለሁለት ወገን ግብርና ቀረጥ ይከፍላል እና ሌሎች መሰል ጉዳዮች ግጭቱ ወይም ጦርነቱ ካመጣቸው መዘዞች በጥቂቱ ናቸው።ይህን ቀውስ በመረዳት ከሰኔ 17 - 19 /2016 አዲስ አበባን ጨምሮ በ8 መድረኮች ችግሩን በትክክል አንስተው የመፍትሄ ሃሳብ ያመጣሉ የተባሉ ከህብረተሰቡ የተውጣጡ ተጽእኖ ፈጣሪ የማህበረሰብ ከፍሎች ጋር ውይይት ተደርጓል።በኋላም በ8ቱ መድረክ በተሳታፊዎች ከተመረጡ የማህበረሰብ ክፍሎች ጋር በባህር ዳር ከተማ ከሰኔ 17 _18 2016 ከሀገሪቱ የጦር ጀኔራሎችና መኮነኖች እንዲሁም የሲቪል አመራሮች ጋር ምክከር ተደርጓል።በመጀመሪያው ዙር በ8ቱ መድረኮች የተነሱ የመፍትሄ ሃሳቦችና በየቀጠናው የተሰጡ የማጠቃለያ መግለጫዎች መለያየትና ቅሬታ የነበረባቸው ቢሆንም በባህርዳሩ ማጠቃለያ መድረክ ግን ከሞላ ጎደል በመድረኩ የተነሳው የመፍትሄ ሃሳብ መግባባትን ፈጥሯል።በዚህ ጉባኤ ጦርነቱ አሸናፊ የሌለው የእርስ በርስ ጦርነት ስለሆነ በንግግርና በውይይት በድርድር ይፈታ የሚል ድምዳሜ ተደርሷል።ይህ ደግሞ በክልል ደረጃ ሊሆን ይችላል ፤በሀገር ደረጃ ሊሆን ይችላል፤ብቻ በየትኛውም መንገድ ይሁን የአማራን ህዝብ ጥቅም ይዠ ነው የምዋጋው ከሚል ሃይል ጋር ያለቅድመ ሁኔታ ንግግርና ድርድር እንዲደረግ የሚል የጉባኤው ማደማደሚያ የመፍትሄ ሃሳብ ነበር።በጉባኤው ማጠቃለያ መንግስት ይህ አሸናፊና ተሸናፊ የሌለው አውዳሚ የእርስ በእርስ ጦርነት በንግግርና በድርድር ለመፍታት ፈቃደኛ ነኝ ነገር ግን ፋኖ አደረጃጀቱና መሪው ብዙ ነው።ለመደራደር አንድ መሆን አለባቸው በማለቱና የድርድሩ ደረጃ ፣ጊዜና ቦታ ተደራዳሪዎች ተለይተው ሁለቱን ወገኖች እያነጋገረ ለንግግርና ለድርድር ጥረት የሚያደርግ 15 አባላት ያሉት አመቻች የሰላም ካውንስል ተመርጧል። ካውንስሉ በርካታ ሃላፊነትና ተግባራት ያሉት ሲሆን ከነዚህ መካከል፦
1. ካውንስሉ በሁለቱም ወገኖች እስካልተመረጠ ድረስ አመቻች እንጂ አደራዳሪ አይደለም ። አመቻች ማለት ሁለቱ ወገኖች እኩል ድርድርና ንግግር እንዲቀበሉ አደራዳሪና ተደራዳሪ እንዲመርጡ ቦታና ጊዜ እንዲወስኑ እያለቀ ያለውን ንጹሃን እየተነዳ ያለው ማህበረሰብ ከፍል ግምት ውስጥ አስገብተው ተኩስ አቁመው እንዲነጋገሩ የማግባባትና የማመቻቸው ስራ ይሰራል ማለት ነው።
2. ካውንስሉ ለየትኛውም ወገን ማዳላት ሳያሳይ በየትኛውም ወገን ጫና ሳይደረግበት ሁለቱም ወገኖች በቅንነት እንዲቀራረቡና እንዲደራደሩ የአመቻችነት ሚናውን ይወጣል።ከየትኛውም ወገን ጣልቃ ገብነት አያስተናግድም።በጉባኤው ማደማደሚያ መስረት ስራውን ይወጣል።
+ ለፌድራል መንግሥት ፣ለአማራ ከልል መንግሥና ለፋኖ ኃይሎች
እየተደረገ ያለው የእርስበርስ ጦርነት ነው።ወንድም ከወንድሙ ልጅ ከአባቱ ጋር መገዳደል ነው። በእርስበርስ ጦርነት የሚባባስ እንጂ የሚፈታ ችግር የለም። በሺ አመታት ተሞከሮ መፍትሄ ያላመጣ የእርስበርስ ጦርነት ዛሬ ለዛውም የዘር፣የብሄርና የሃይማኖት አዝማሚያ ታክሎበት የሚደረግ የእርስበርስ ጦርነት ከመተላለቅ ውጪ አንዳችም መፍትሄ ሊያመጣ አይችልም።ለአኛ ለኢትዮጵያውያን ሰበር ዜና ሊሆን የሚችለው መፍትሄ የማያመጣ የእርስበርስ ጦርነት ማድረጋችን ሳይሆን ከመገዳደል ወጥተን ፖለቲካዊ ልዩነታችን በውይይት፣ በመነጋገር፣ በመደራደርና በሰጥቶ መቀበል በሚፈታ የፖለቲካ አውድ ውስጥ ስንገባና ባህል ስናደርግ ያኔ ነው ለኢትዮጵያ ሰበር ዜና መባል ያለበት። ስለሆነም የወገናችሁ ስቃይ ተረድታችሁ መሸናነፍ በማትችሉበት ጦርነት ከመቆየት ሁለታችሁም ማሸነፍ ወደ ምትችሉበት ንግግርና ድርድር እንድትገቡ አመቻች የሰላም ካውንስሉ አበክሮ ይጠይቃል፣ለማግባባትም ይጥራል።
አንደኛ ለፌደራል መንግስትና ለአማራ ከልል መንግስት መግለጽ የምንፈልገው ይህ የሰላም ካውንስል ሲቋቋም በርቱ፣ሞክሩ ከጎናችሁ ነን የሚሉ ወገኖች እንዳሉ ሁሉ በሌላ ወገን ደግሞ ለሌላ አላማ ወይም ለአለም አቀፍ ማህበረሰብ ለማስመሰል ካልሆነ በስተቀር እናንተ የምትሉት መንገድ መንግስት የሚቀበለው አይመስለንም ብለው ስጋታቸውን ሲገልጹ ይሰማል።እርግጥ ሲሆን ከኖረውና እየሆነ ካለው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ባህል አንጻር የሚጠበቅ አባባል ቢሆንም የህዝባችን ስቃይ አይተን በቅንነት ለምናቀርበው ሃሳብ መንግሥት በቅንነት ተረድቶ ቀጥታ በንግግርና በድርድር የእርስበርስ ጦርነት የምናቆምበት መንገድ ብቻ እንድናተኩር ከመንግስት መታመንን የሰላም ካውንስሉ በትልቁ ይጠብቃል።
ሁለተኛ ለፋኖ ወንድሞቻችንም አጥብቀን ማሳሰብ የምንፈልገው ህዘባችሁ ያለበት ስቃይ ተረድታችሁ አሸናፊና ተሸናፊ በሌለው ጦርነት ከመቀጠል ሁሉንም አሸናፊ ሊያደርግ የሚችለው የድርድር መርህ ተቀበላችሁና ተከትላችሁ እንታገልለታለን የምትሉትን የህዝብ አጀንዳ በንግግርና ድርድር ለመፍታት ቁርጠኛ እንድትሆኑ እንጠይቃለን።
+ ለፓለቲካ ፓርቲ መሪዎች፣ለምሁራንና ለማህበራዊ ሚዲያ አንቂዎች፤ ለመላው የአማራ ክልል ነዋሪና ለቀሪው የሃገራችን ህዝብ ከፍል፤በውጭ ሀገር ለምትኖሩ የአማራ ክልል እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሙሉ
የአማራ ከልል ወገናችሁ በተፈጠረው የእርስ በእርስ ጦርነት ስቃይ ውስጥ ነው ብለን ስንነግራችሁ ሰምተን ሳይሆን አይተንና መከራና ስቃዩ ግድያው አልፎብን ነው። በመጀመሪያ ደረጃ በ21ኛው ክ/ዘመን አስቀያሚ ጦርነት እያደረግን ያለነው ሰላማዊ ትግል እግር ባለመትከሉና ህዝቡ ከጦርነት ይልቅ ሰላማዊ ትግል እንዲከተል ያልሆነው ሁላችንም የየራሳችን የድከመት ድርሻ አለብን ብለን አለማመናችን ነው።የእርስ በርስ ጦርነት እየተፈጠረ ያለው በሰላማዊ ትግል የሚያምን ፖለቲካል ማህበረሰብ አለመፈጠሩ ነው ።የፈለገውን ያህል ጦርነት ቢካሄድ ወጣቱ ካለቀ በኋላ አዋጊዎች ወደ ድርድር እንደሚመጡ ከሰሜኑ ጦርነት መማር ያስፈልጋል።ስለሆነም በእናንተ በኩል ስቃይ ውስጥ ያለውን ማህበረሰብ የእርስ በርስ ጦርነት ማባባስ ሳይሆን ሁለቱ ወገኖች ንግግርና ድርድር የሚያስቀድሙበትን መንገድ ውስጥ እንዲገቡ መገፋፋት ማበረታታትና ማገዝ ትልቁ ድርሻቸሁ እንዲሆን እንጠይቃለን።
በመጨረሻም ሰላም የግለስብ ፤የአርሶ አደሩና የአርብቶ አደሩ፤የተማሪዎች ፤የሴቶችና የወንዶች የሃይማኖት አባቶች የባለሃቶች፣የአንድ ክልል ህዝብ ፤የመንግስት ሃይሎች፤ጭካ የገቡ የፋኖ አባላት የብቻ ጉዳይ አይደለም።ሰላም የሁሉም ከሁሉም ነው።ስለሆነም በየደረጃው ጥሪ የተደረገላችሁ አካላት የበኩላችሁን እንድትወጡና ይህ የሰላም ጥሪያችን በአዎንታዊ መልኩ ታይቶ የሀገራችንን ሰላም በጋራ እናምጣ፣ የወንድማማቾች መገዳደል ይብቃ በማለት የአማራ ክልል የሰላም ካውንስል ጥሪውን ያቀርባል።