የአማራ ክልል አመቻች የሰላም ካውንስል መንግስትና በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ተኩስ አቁመው ለውይይትና ድርድር እንዲቀመጡ ጥሪ አቀረበ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 22/2016(ኢዜአ)፦ የአማራ ክልል አመቻች የሰላም ካውንስል መንግስትና በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ተኩስ አቁመው ለውይይትና ድርድር እንዲቀመጡ ጥሪ አቀረበ።

በአማራ ክልል የተከሰተውን የሰላም እጦት ለመፍታት ሰኔ 17 እና 18 ቀን 2016 በባህርዳር የህዝብ ተወካዮች ምክክር አድርገዋል።

በዚህም ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት መንግስትና በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎችን ለማመቻቸት 15 አባላት ያሉት የማህበረሰብ ተወካዮች ተመርጠው የአማራ ክልል አመቻች የሰላም ካውንስል ተቋቁሟል።

አመቻች የሰላም ካውንስሉ በአማራ ክልል ለአንድ ዓመት የዘለቀውን ግጭት ለመፍታት ሁሉም ተፋላሚ ሀይሎችን ለማወያየት መዘጋጀቱን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።

ካውንስሉ በኢትዮጵያ በእርስ በርስ ጦርነት የተፈታ ችግርም የመጣ መፍትሔም እንደሌለ ገልጿል።

በመሆኑም የፌዴራልና የአማራ ክልል መንግስት እና በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች መካከል የተከሰተው አለመግባባት በውይይት እንዲፈታ ጠይቋል።

መንግስት እና በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች ለሰላም ውይይት እና ለድርድር ዝግጁ መሆናቸውን በመግለጫ እንዲያሳውቁም ጥሪ አቅርቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም