ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ባለፉት ጊዜያት ለተፈጸሙ በደሎች በሽግግር ፍትህ ምላሽ መስጠት ይገባል - ተስፋዬ በልጅጌ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 22/2016(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ባለፉት ጊዜያት ለተፈጸሙ በደሎች እና የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በሽግግር ፍትህ አማካኝነት ተገቢውን ምላሽ መስጠት እንደሚገባ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ(ዶ/ር) ገለጹ።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በሽግግር ፍትህ ፖሊሲ እና በፌዴራል አስተዳደራዊ ስነ-ስርአት አዋጅ ላይ ውይይት አድርገዋል።


 

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ(ዶ/ር) በውይይቱ ወቅት እንደገለጹት ሀገራዊ ምክክር እና የሽግግር ፍትህ ተመጋጋቢ እንደሆኑና ኢትዮጵያን ካለችበት ችግር ማውጣት የሚያስችሉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የተለያዩ ሀገራት የሽግግር ፍትህ ፖሊሲን ተግባራዊ በማድረግ ከፀረ ዲሞክራሲ ወደ ዲሞክራሲ ስርአት፣ ከእርስ በርስ ግጭት ወደ ተረጋጋ ሀገረ መንግሥት ምስረታ እንደተሽጋገሩም ተስፋዬ በልጅጌ(ዶ/ር) አስረድተዋል።

በመሆኑም ኢትዮጵያ የሽግግር ፍትህ ፖሊሲን ተግባራዊ በማድረግ ካጋጠማት የግጭት አዙሪት ተላቃ ሁሉንም የሚያግባባ ሀገረ መንግሥት መመሰረት እንደሚገባ ነው የመንግሥት ዋና ተጠሪው ያስገነዘቡት።

በዚህም የሕግ ተጠያቂነትን ማስፈን፣ እውነትን ማረጋገጥ፣ የተጎዱትን መጠገን ወይም የማካካሻ ስርዓት ማበጀትና ተገቢውን ክብር መስጠት፣ ተመሳሳይ በደሎች እንዳይከሰቱ መከላከልና ብሔራዊ መግባባቶችን ማሳለጥ በዚሁ ማዕቀፍ የሚታይ መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም ለፖሊሲው ውጤታማነት የምክር ቤቱ አባላትና ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በሌላ በኩል በየጊዜው የሚወጡ ህጎችና መመሪያዎች በአግባቡ ተግባራዊ ባለመሆናቸው ህዝቡ ለመልካም አስተዳደር ችግር እየተዳረገ በመሆኑ ተገቢውን ክትትልና ቁጥጥር ማድረግ እንደሚገባ ማሳሰባቸውን ከምክር ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም