የመቻል ስፖርት ክለብ 80ኛ ዓመት የምስረታ በዓልን አስመልክቶ የተዘጋጀ የፓናል ውይይት እየተካሄደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የመቻል ስፖርት ክለብ 80ኛ ዓመት የምስረታ በዓልን አስመልክቶ የተዘጋጀ የፓናል ውይይት እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 22/2016(ኢዜአ)፦ መከላከያ ሚኒስቴር የመቻል ስፖርት ክለብ 80ኛ ዓመት የምስረታ በዓልን በማስመልከት ያዘጋጀው የፓናል ውይይት በመካሄድ ላይ ይገኛል።
በውይይቱ ላይ የመከላከያ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሐመድ፣ የሀገር መከላከያ ሰራዊት የስነ ልቦና ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጀነራል እንዳልካቸው ወልደኪዳን፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን፣ የክለቡ አንጋፋና አሁን ላይ እየተወዳደሩ ያሉ ስፖርተኞችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
የመከላከያ ሚኒስቴር የመቻል ስፖርት ክለብን 80ኛ የምስረታ በዓልን "መቻል ለኢትዮጵያ" በሚል መሪ ሀሳብ እያከበረ ይገኛል።
የመቻል የምስረታ በዓል አካል የሆነ የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድር ነገ በመስቀል አደባባይ እንደሚካሄድ ይታወቃል።
ሰኔ 30 ቀን 2016 ዓ.ም የመንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና ባለሀብቶች በተገኙበት የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር ይከናወናል።
የ37 ዓመቱ የፖርቹጋል ብሔራዊ ቡድን እና የማንችስተር ዩናይትድ ተጫዋች ሉዊስ ካርሎስ አልሜይዳ ዳ ኩንሃ(ናኒ) ሐምሌ 6 ቀን 2016 ዓ.ም የምስረታ በዓሉን በማስመልከት ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጣ መገለጹ ይታወሳል።
በተጨማሪም መቻል በዩጋንዳ ፕሪሚየር ሊግ ከሚጫወተው ኪታራ ክለብ ጋር ሐምሌ 7 ቀን 2016 ዓ.ም የወዳጅነት ጨዋታ ያደርጋል።
የመቻል ስፖርት ክለብ በ1936 ዓ.ም የተመሰረተ ሲሆን በእግር ኳስ፣ በአትሌቲክስ፣ ቦክስና ሌሎች ስፖርቶች ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ የስፖርት መድረክ ወክለው ውጤታማ የሆኑ ስመጥር ስፖርተኞች አፍርቷል።