ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በተገኙበት በተለያዩ መርሐ-ግብሮች ያሰለጠናቸውን የፖሊስ መኮንኖች አስመረቀ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 22/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በተገኙበት በተለያዩ መርሐ-ግብሮች ያሰለጠናቸውን የፖሊስ መኮንኖችን አስመረቀ።

በምረቃ መርሐ-ግብሩ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ የዩኒቨርሲቲው የቦርድ ሰብሳቢና የስራ እና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል፣ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፈንታ፣ ከፍተኛ የፖሊስ መኮንኖችን ጨምሮ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል።


 

ዩኒቨርሲቲው ዛሬ ያስመረቃቸው የፖሊስ መኮንኖች በሁለተኛ ዲግሪ፣ በመጀመሪያ ዲግሪ፣ በሌቭል አራት እና በጤና ሳይንስ እንዲሁም በሌሎች የትምህርት ዘርፎች የሰለጠኑ ናቸው ተብሏል።

ዩኒቨርሲቲው ያስመረቃቸው የሁለተኛ ዲግሪ ተመራቂ መኮንኖች በአራት ፕሮግራሞች ትምህርታቸውን የተከታተሉ ሲሆን በስነ ወንጀልና በወንጀል ፍትህ፣ በሰላምና የህዝብ ደህንነት ጥናት፣ በአስተዳደር እና የለውጥ አመራር እንዲሁም በደህንነት ዘርፍ አስተዳደር የሰለጠኑ መሆናቸውም ተገልጿል።

ዩኒቨርሲቲው በደህንነት ዘርፍ አስተዳደር ለመጀመሪያ ጊዜ አስተምሮ ማስመረቁም በዚሁ ወቅት ተጠቁሟል።

ሰልጣኞች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ፖሊሳዊ ሳይንስ፣ በስነ-ወንጀልና ወንጀል ፍትሕ እንዲሁም በፖሊስ መኮንንነት ዘርፍ አስፈላጊውን ሙያና እውቀት የጨበጡ መሆናቸውም ተገልጿል።

ዩኒቨርሲቲው ዛሬ ካስመረቃቸው ሰልጣኞች መካከል ሲያሰለጥናቸው የቆዩ 12 የሶማሊያ እና የደቡብ ሱዳን የፖሊስ ሰልጣኞች ይገኙበታል።

ዩኒቨርሲቲው በተለያዩ የፖሊስ የሙያ መስኮች ከአጫጭር ኮርሶች እስከ ሁለተኛ ዲግሪ በማስተማር በኢትዮጵያ እና በምስራቅ አፍሪካ ብቁ የሆኑ የፖሊስ መኮንኖችን እና ባለሙያዎችን በማፍራት ላይ እንደሚገኝም ተጠቁሟል።

የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ በኢትዮጵያ የፖሊስ ሰራዊት ግንባታ ውስጥ ደማቅ አሻራ ያኖረ ረጅም ዘመናትን የቆየ አንጋፋ ተቋም ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም