በዞኖቹ የደረሰ የበልግ ሰብል በተቀናጀ የህዝብ ተሳትፎ እየተሰበሰበ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በዞኖቹ የደረሰ የበልግ ሰብል በተቀናጀ የህዝብ ተሳትፎ እየተሰበሰበ ነው
ዲላ፤ ሰኔ 22/2016 (ኢዜአ)፡-በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ቡርጂ እና ኮሬ ዞኖች የደረሰ የበልግ ሰብል በተቀናጀ የህዝብ ተሳትፎ እየተሰበሰበ መሆኑን የዞኖቹ ግብርና መምሪያዎች አስታወቁ።
የደረሰ የበልግ ሰብል በተሰበሰበባቸው የእርሻ ማሳዎች ለመኸር እርሻ ዝግጅት መጀመራቸውንም አርሶ አደሮች ገልጸዋል።
የቡርጂ ዞን ግብርና መምሪያ የእርሻ ዘርፍ ሃላፊ አቶ ደረሰ ዳይጎ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ በዞኑ ሁሉንም አቅሞች አሟጦ በመጠቀም በበልግ እርሻ ከ85 ሺህ 830 ሄክታር በላይ መሬት በዘር ለመሸፈን ተችሏል።
ከዚህ ውስጥ ከ56 ሺህ 860 ሄክታር በላይ ማሳ በኩታገጠም ጤፍ የለማ ሲሆን በቆሎ፣ ማሽላ እና ስንዴም በስፋት መልማቱን አስረድተዋል።
በኩታገጠም የተሳተፉ አርሶ አደሮች እስካሁን ድረስ በ48 ሺህ 331 ሄክታር ላይ የለማ ሰብል በጋራ በማንሳት ከ386 ሺህ 648 ኩንታል ምርት መሰብሰባቸውን ተናግረዋል።
በቀጣይ ሁለት ሳምንታት የደረሱ ሰብሎችን በተለይ በቆሎን በስፋት በማንሳት በሙሉ አቅም ወደ መኸር እርሻ ዝግጅት ለመግባት እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።
የዞኑን ትርፍ የማምረት አቅም በአግባቡ ለመጠቀም በበልግ እርሻ ሰፊ ርብርብ መደረጉን ያነሱት ደግሞ የኮሬ ዞን ግብርና መምሪያ የእርሻ ዘርፍ ሃላፊ አቶ አሰፋ ዓለማየሁ ናቸው።
በዚህም ከ65 ሺህ 587 ሄክታር በላይ መሬት በዘር ለመሸፈን መቻሉን ጠቅሰው፣ ከ1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅም ጠቅሰዋል።
እስካሁን በ33 ሺህ 162 ሄክታር ላይ የደረሰ ሰብል በማንሳት ከ295 ሺህ 447 ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ተችሏል ብለዋል።
የደረሰ ስብል ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብና ተባይ እንዳይበላሽም አርሶ አደሩ በቡድን ምርት የመሰብሰብ ሥራውን አጠናክሮ መቀጠሉንም አቶ አሰፋ አስረድተዋል።
በቡርጂ ዞን ሶያማ ዙሪያ ወረዳ ነደሌ ዳሌ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር አለማየሁ ዋዳኮ በበኩላቸው በበልግ እርሻ እሳቸውን ጨምሮ ከ20 በላይ አርሶ አደሮች ከ54 ሄክታር በላይ ማሳ በኩታ ገጠም ማልማታቸውን ጠቅሰዋል።
የኩታ ገጠም የሰብል ልማት የግብዓትና የሙያ ድጋፍ በቅርበት እንዲያገኙ ከማድረግ ባለፈ የደረሰ ሰብልን በጋራ ለመሰብሰብ ማስቻሉን ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅትም በሦስት ሄክታር ማሳቸው ላይ የነበረን ጤፍ በህብረት የማጨድና የመውቃት ሥራ እያከናወኑ መሆናቸውን አስረድተዋል።
አምና ከሄክታር 12 ኩንታል ምርት ማግኝታቸውን ያስታወሱት አርሶ አደሩ፣ ዘንድሮ የተስተካከለ የዝናብ ስርጭትና የተሻለ የግብዓት አጠቃቀም በመኖሩ የተሻለ ምርት እንደሚጠብቁ ተናግረዋል።
በበልግ የለማውን ሰብል አንስተው ለመኸር እርሻ ዝግጅት መጀመራቸውን የገለጹት ደግሞ በኮሬ ዞን ጎርካ ወረዳ የዳኑ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር እያሱ ጨነቀ ናቸው።
በቀጣይ የመኸር አዝመራ ቦሌቄ ለመትከል የዘርና የማሳ ዝግጅት መጀመራውንም አመልክተዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ የእርሻ ዘርፍ ሃላፊ አቶ አድማሱ አወቀ በበኩላቸው በክልሉ በበልግ እርሻ ከ797 ሺህ 760 ሄክታር በላይ ማሳ በዘር መሸፈኑን ተናግረዋል።
በበልግ እርሻ እንቅስቃሴ ክልሉ ሰፊ አቅም እንዳለው የጠቆሙት ሃላፊው፣ ከዘንድሮ የበልግ ልማትም ከ68 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይጠበቃል ብለዋል።
ሰብል ቀድሞ በደረሰባቸው የክልሉ አካባቢዎች ምርት የመሰብሰብ ሥራ በስፋት እየተከናወነ እንደሚገኝም ተናግረዋል።