ቀጥታ፡

ቅዱስ ጊዮርጊስና ኢትዮጵያ ቡናን በፕሪሚየር ሊጉ ለ48ኛ ጊዜ የሚያገናኘው የደርቢ ጨዋታ ተጠባቂ ነው

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 22/2016(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ29ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ቅዱስ ጊዮርጊስና ኢትዮጵያ ቡና ዛሬ የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል።

የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ከምሽቱ 12 ሰዓት በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይካሄዳል።

በጊዜያዊው አሰልጣኝ ደረጀ ተስፋዬ እየተመራ የሚገኘው ቅዱስ ጊዮርጊስ በዘንድሮው ፕሪሚየር ሊግ ጥሩ ጊዜ እያሳለፈ አይደለም።

ፈረሰኞቹ በውድድር ዓመቱ እስከ አሁን 28 ጨዋታዎችን አድርገው 12 ጊዜ ሲያሸንፉ 8 ጊዜ ተሸንፈዋል፤ 8 ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥተዋል።

በ28ቱ ጨዋታዎች 38 ጎሎችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ 25 ጎሎችን አስተናግዷል። 

ቅዱስ ጊዮርጊስ በሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት 5 ተከታታይ ጨዋታዎች ያሸነፈው 1 ጊዜ ብቻ ሲሆን፤  2 ጊዜ ሲሸነፍ 1 ጊዜ አቻ ወጥቷል።

በነዚህ 5 ጨዋታዎች 5 ጎሎችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ 4 ግቦችን አስተናግዷል፤ ቅዱስ ጊዮርጊስ በ44 ነጥብ 5ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

በአንጻሩ ተጋጣሚው ኢትዮጵያ ቡና በውድድር ዓመቱ መልካም የሚባል ግስጋሴ እያደረገ ይገኛል።

ቡናማዎቹ በሊጉ ባደረጓቸው 28 ጨዋታዎች በ14ቱ ድል ሲቀናቸው 6 ጊዜ ተሸንፈዋል፤  8 ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥተዋል።

ቡድኑ በ28ቱ ጨዋታዎች ላይ 49 ጎሎችን ሲያስቆጥር 29 ጎሎችን አስተናግዷል።

በነጻነት ክብሬ የሚሰለጥነው ኢትዮጵያ ቡና ያለፉትን 5 የሊግ ጨዋታዎች አሸንፏል፤  በ5ቱ ጨዋታዎች 16 ግቦችን ሲያስቆጥር 4 ጎሎች ተቆጥረውበታል።

ኢትዮጵያ ቡና በ50 ነጥብ 3ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ቅዱስ ጊዮርጊስና ኢትዮጵያ ቡና በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሲገናኙ የአሁኑ ለ48ኛ ጊዜ ነው። 

ክለቦቹ ከዚህ ቀደም ባደረጓቸው 47 ጨዋታዎች ቅዱስ ጊዮርጊስ 21 ጊዜ በማሸነፍ የበላይነቱን የያዘ ሲሆን ኢትዮጵያ ቡና 8 ጊዜ አሸንፏል፤ 18 ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥተዋል።

በ47ቱ ጨዋታዎች ቅዱስ ጊዮርጊስ 62 ግቦችን ሲያስቆጥር ኢትዮጵያ ቡና 31 ግቦችን ከመረብ ላይ አሳርፏል።

የሁለቱ ክለቦች ደጋፊዎች ለጨዋታው ተጨማሪ ድምቀት ይሰጡታል ተብሎ ይጠበቃል።

ሁለቱ ክለቦች በፕሪሚየር ሊጉ በመጀመሪያ ዙር ባደረጉት ጨዋታ ጫላ ተሺታ ባስቆጠራት ግብ ኢትዮጵያ ቡና 1 ለ 0 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።

በ29ኛ ሳምንት ሌላኛው መርሐ ግብር ወላይታ ድቻ ከፋሲል ከነማ ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ወላይታ ድቻ በ33 ነጥብ 13ኛ እንዲሁም ፋሲል ከነማ በ43 ነጥብ 7ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።

ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያ ዙር ባደረጉት ጨዋታ ወላይታ ድቻ 2 ለ 0 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።

በተያያዘም በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ትናንት በተደረገ ጨዋታ ኢትዮጵያ መድን ሀድያ ሆሳዕናን 1 ለ 0 አሸንፏል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም