ቀጥታ፡

ምክር ቤቱ  አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ለሚያከናውናቸው ስራዎች አስፈላጊውን ድጋፍና እገዛ ያደርጋል - አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 21/2016(ኢዜአ)፡- የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ለሚያከናውናቸው ስራዎች አስፈላጊውን  ድጋፍና እገዛ እንደሚያደርግ የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ገለጹ።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአገራዊ ምክክር ኮሚሽን የአፈጻጸም ደረጃና በቀጣይ አቅጣጫ ላይ ተወያይቷል።

በመድረኩ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ፣ የፍትህ ሚኒስትር ጌድዮን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር)፣ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር)፣ የአገራዊ ምክክር ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያና የምክርቤቱ አባላት ታድመዋል።

የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ የምክክር ኮሚሽኑን አፈጻጸም ለምክር ቤቱ አባላት አብራርተዋል።


 

የምክር ቤቱ አባላት በሰጡት አስተያየት፤ ኮሚሽኑ አሳታፊነትን ለማረጋገጥ የሄደበት ርቀት ጥሩ መሆኑን ገልጸዋል። 

በተጨማሪም በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥም ያከናወነው ስራ የሚያስመሰግን መሆኑንና በቀጣይም ሊታገዝ እንደሚገባ አመልክተዋል።


 

በቀጣይም በተለያዩ ምክንያቶች ስራዎች ያልተሰሩባቸው አካባቢዎች ላይ ትኩረት በማድረግ መስራት እንዳለባቸው ገልጸዋል።

አባላቱ የምክክር ኮሚሽኑ በአገሪቱ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን ለመፍታትና  በመነጋገር የሚያምን ትውልድ ለመፍጠር መሰረት የሚጥል መሆኑን ጠቁመዋል።



በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) ኮሚሽኑ ያከናወናቸው ስራዎች ውጤታማ መሆናቸውንና ለዚህም እውቅና መስጠት ይገባል ብለዋል።

በተቻለ አቅም አገራዊ   ምክክሩ ስኬታማ እንዲሆን ሁሉም ኢትዮጵያውያን ኮሚሽኑን ሊያግዝ እንደሚገባ አመላክተዋል።

መንግስት የዴሞክራሲ ምህዳሩ እንዲሰፋ አስቻይ ሁኔታ እንዲኖር የተለያዩ እርምጃዎችን መውሰዱንና ውጤቶች እየተመዘገቡ መሆኑን ገልጸዋል።

የምክርቤቱ አባላት ኮሚሽኑ እያከናወነ ያለውን ስራ ለመረጣቸው ህዝብ ግንዛቤ ሊያስጨብጡ እንደሚገባና የደረሰበትን ደረጃ ሊያሳውቁ እንደሚገባ አመላክተዋል።


 

የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ ምክክሩ አካታች እንዲሆን ከፍተኛ ስራ መሰራቱን ገልጸዋል።

ኮሚሽኑ የሚፈጠሩ ብዥታዎችን በመፍታት በገለልተኛነት ስራውን እያከናወነ መሆኑን ጠቀመው፤ ኮሚሽኑ የትኛውንም አስተያየት ለመቀበል በሩ ክፍት መሆኑን ገልጸዋል።

በአዲስ አበባ የተካሄደው የምክክር ምዕራፍ ስኬታማና በቀጣይ ኮሚሽኑ ለሚያከናውነው ስራ መሰረት መሆኑን ተናግረዋል።

በቀጣይ ለሚከናወኑ ስራዎችና የሴቶች ተሳትፎ እንዲያድግ የምክር ቤቱ አባላት አስፈላጊውን እገዛ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ የአገራዊ ምክክር አዋጅ አሳታፊ እንዲሆን በጥንቃቄ መዘጋጀቱን አስታውሰዋል።

ምክክሩ የተሳካ እንዲሆን በቅንነት መስራት እንደሚገባና ሁሉም ወደዚህ ምክክር መምጣት እንዳለበት አስገንዝበዋል

ምክር ቤቱ የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን በቀጣይ ለሚያከናውናቸው ስራዎች አስፈላጊው ድጋፍ እና እገዛ እንደሚያደርግ አመላክተዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም