ቀጥታ፡

በመዲናዋ የሚገኙ የ12ተኛ ክፍል የኦንላይን ተፈታኞች ከነገ ጀምሮ የተግባር ልምምድ ማድረግ ይጀምራሉ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ  21/2016(ኢዜአ)፦በኦንላይን ፈተና የሚወስዱ የ12ተኛ ክፍል ተማሪዎች የተግባር ልምምድ የሚያደርጉበት የመለማመጃ ፈተና ከነገ ሰኔ 22 ጀምሮ እንደሚሰጥ የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።

የሚደረገው ልምምድ የመፈተኛ ጣቢያዎች የኦንላይን ፈተናውን ለመስጠት ያላቸውን አቅም ለማረጋገጥ የሚረዳ መሆኑም ተገልጿል።

የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዘላለም ሙላቱ ለኢዜአ እንዳሉት በከተማ አስተዳደሩ የ2016 ዓም የ12ተኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና በኦንላይንና በወረቀት ለመስጠት የቅድመ ዝግጅት ስራ እየተጠናቀቀ ይገኛል። 

የኦንላይን ፈተናው በአይነቱ አዲስ በመሆኑ ተማሪዎች እንዲረዱት እንዲሁም የመፈተኛ ጣቢያዎች የማስፈፀም አቅምና ምቹና ሳቢ መሆናቸውን የማረጋገጥ ስራ ከነገ ጀምሮ እስከፈተናው መዳረሻ ድረስ ይሰራል ብለዋል።   

የሚደረገው የሙከራ ፈተና አሰጣጥ ሂደት የኢንተርኔት ፍጥነትና አቅም፣ የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት ዘላቂና አስተማማኝነት ለማረጋገጥ የሚረዳ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ተማሪዎች ከቴክኖሎጂው ጋር የማላመድ ሂደት ለመመልከትና በፈተና ጣቢያዎች የሚኖሩ ችግሮችን በመለየት ለመፍታት የሚያስችል መሆኑንም ተናግረዋል።        

በአብርሆት ቤተመፃህፍት ከ3ሺህ በላይ ታብሌቶች የመሰረተልማት ዝርጋታ ስራ በማከናወን ተማሪዎችን በነገው እለት  መዘጋጀታቸውንም ተናግረዋል።

በአዲስ አበባ ደረጃ ያሉ 163 መፈተኛ ጣቢያዎች የአቅም በመፈተሽ ከነገ ጀምሮ እስከፈተናው ሳምንት ድረስ የጣቢያዎችን አቅም የማጠናከርና የሚታዩ ጉድለቶችን የማስተካከል ስራ ይሰራል ነው ያሉት።

በፈተና ወቅት አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት እንዲኖር ከሚመለከተው ተቋም ጋር በቅንጅት ከመስራት በተጨማሪ በሁሉም መፈተኛ ጣቢያዎች የጄኔሬተር  አቅርቦት እንዲኖር ተሰርቷል ብለዋል።

የኦንላይን ፈተና ሂደቱ አስተማማኝ እንዲሆን ለማድረግ በመፈተኛ ጣቢያዎች የተደረገው ቅድመዝግጅት ተማሪዎችም የሚኖርባቸውን ስጋት በማስወገድ ፈተናውን በተመቸ አግባብ እንዲወስዱ የሚያስችል መሆኑን ጠቁመዋል።

የፈተና ሂደቱ ውጤታማ እንዲሆን ባለድርሻ አካላት ሚናቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል።

በዘንድሮ አመት በአዲስ አበባ ደረጃ የ12ተኛ ክፍል ፈተና ከሚወስዱ 50ሺህ በላይ ተማሪዎች መካከል 28ሺህ ያህሉ በኦንላይን ፈተና እንደሚወስዱም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም