በቡና ልማትና ግብይት ላይ የሚሰሩ ተዋንያንን በማገናኘት የዘርፉን ችግሮች ለመፍታት እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በቡና ልማትና ግብይት ላይ የሚሰሩ ተዋንያንን በማገናኘት የዘርፉን ችግሮች ለመፍታት እየተሰራ ነው
ሀዋሳ፤ ሰኔ 21/2016 (ኢዜአ) -በቡና ልማትና ግብይት ላይ የሚሰሩ ተዋንያንን በማገናኘት የዘርፉን ችግሮች ለመፍታት የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን አስታወቀ።
ቡና አምራች በሆኑ አራት ክልሎች የሚገኙ የቡና አምራች፣ አቅራቢ እና ላኪዎችን ያገናኘ የቡና አውደ ርዕይ በሀዋሳ ከተማ ዛሬ ተከፍቷል።
በአውደ ርዕዩ መክፈቻ ላይ የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዱኛ ደበላ፣ የቡና አምራቾች፣ አቅራቢዎችና ላኪዎችን በዘርፉ የሚያነሷቸውን ችግሮች ለመፍታት ታስቦ አውደ ርዕዩ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።
''በቡና ንግድ ሂደት ውስጥ አምራች፣አቅራቢና ላኪ ብዙም አይተዋወቁም ነበር'' ያሉት ዶክተር አዱኛ አውደ ርዕዩ እነዚህን አካላት በማገናኘት ትልቅ ፋይዳ አለው ብለዋል።
አውደ ርዕዩ የገበያ እድልን በማስፋት ምርትና ምርታማነት ላይ ለውጥ ለማምጣት እንደሚያግዝም ተናግረዋል።
በዚህ አውደ ርዕይ ላይ ከ300 የሚበልጡ ቡና አብቃይ ከሆኑ ኦሮሚያ፣ ሲዳማ፣ ደቡብ ኢትዮጵያና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልሎች የተውጣጡ ቡና አምራች ማህበራት፣ አቅራቢዎችና ላኪዎች ተሳታፊ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ቡና አቅራቢና ላኪዎች ቀጣይ በጋራ ለመስራት የሚያስችል ስምምነት የሚፈራረሙበት ሁኔታና ትስስር እንደሚፈጠርም ዶክተር አዱኛ አስታውቀዋል።
ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አሪ ዞን ሰሜን አሪ ወረዳ የመጡት ቡና አቅራቢ አቶ ኩኩ መኮንን፣አውደ ርዕው በዞኑ የሚመረተውን ቡና በአካባቢው ስያሜ ለማስተዋወቅና ለውጪ ገበያ ለማቅረብ የራሱ አስተዋጾ ይኖረዋል ብለዋል።
ሙለጌ ሀላፊነቱ የተወሰነ ቡና ላኪ ድርጅት ባለቤት አቶ ሙስጠፋ አወል በበኩላቸው ''አውደ ርዕዩ ከቡና አምራችና አቅራቢ ድርጅቶች ጋር እንድንተዋወቅ እድል ከመፍጠሩ ባለፈ ለውጪ ገበያ የሚቀርበውን ቡና ጥራት ለማስጠበቅ ትልቅ ፋይዳ አለው'' ብለዋል።
''በቡና ንግድ ዙሪያ ባለው ችግርና ጥራት ዙሪያ በአቅራቢው ዘንድ ያለውን ችግር እኛ እንጠቁማለን፣ በእኛ በኩል ያለውን ቅሬታ ከአቅራቢዎች ሰምተን ጥሩ ስራ ለመስራት ትስስር መፍጠር እንድንችል ያግዘናል'' ነው ያሉት።
በነገው ዕለት በቡና ጥራት ዙሪያ ውይይት እንደሚደረግ ተገልጿል።