በድሬዳዋ አስተዳደር 17 ሺ ለሚጠጉ ሰዎች ቋሚ የስራ ዕድል ተፈጥሯል-ቢሮው

 ድሬዳዋ፤ ሰኔ 21/2016 (ኢዜአ)፦ በድሬዳዋ አስተዳደር ገጠርና ከተማ 17 ሺ ለሚጠጉ ሰዎች  ቋሚ የስራ ዕድል መፈጠሩን የአስተዳደሩ የስራ ክህሎትና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ  አስታወቀ።

በአስተዳደሩ በስራ እድል  ፈጠራ የተጀመሩ ተግባራትን በላቀ ደረጃ ለማሳደግ በተወጠነ አቅጣጫ ላይ ለዘርፉ አመራሮች ስልጠና ተሰጥቷል ።


 

የቢሮው ኃላፊ አቶ ሮቤል ጌታቸው በስልጠናው ላይ እንዳሉት  በድሬዳዋ አስተዳደር በበጀት አመቱ በገጠርና በከተማ በተለያዩ ዘርፎች ለ18ሺ 330 ሰዎች  ቋሚ የስራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ ለ16 ሺ995 ሰዎች  እድሉ ተፈጥሮላቸዋል ።

በአፈጻጸሙም የዕቅዱን 93 በመቶ ማሳካት መቻሉን አመልክተዋል ።

የስራ ዕድሉ የተፈጠረው በ520 አዲስና ነባር ኢንተርፕራይዞችና ማደራጀት አማካኝነት  በግብርና ፣ በኢንዱስትሪና  በአገልግሎት ዘርፎች መሆኑን አብራርተዋል።

በተጨማሪም መንግስታዊና መንግስታዊ ባልሆኑ ተቋማት እንዲሁም በህብረት ስራ ማህበራት የስራ ዕድሉ መፈጠሩን  ጠቅሰዋል። ።

እንደ አቶ ሮቤል ገለፃ በበጀት አመቱ የስራ ዕድል ከተፈጠረላቸው መካከል  ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ ከቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች የተመረቁ ወጣቶች ይገኙበታል ።

"በየደረጃው ለሚገኙ የዘርፉ አመራሮች የተሰጠው ስልጠና በዘርፉ የተጀመረውን ስራ በተቀናጀና በተናበበ መንገድ አጠናክሮ ለማስቀጠል ያስችላል" ብለዋል።

የድሬዳዋ አስተዳደር የስራ ክህሎትና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ ፈጡም ሙስጠፋ በበከላቸው ከሚቀጥለው በጀት አመት ጀምሮ ለወጣቶች የሚሰጠው  ክህሎት መር ስልጠና በገበያ ውስጥ ተወዳዳሪና አሸናፊ የሚያደርጋቸው መሆኑን ገልጸዋል ።

በተጨማሪም ከቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ክህሎት መር ስልጠና ቀስመው  የሚወጡ ወጣቶች ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች የስራ ዕድል የሚፈጥሩበትን አቅጣጫዎችን ያካተተ መሆኑን ተናግረዋል ።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም