12ተኛው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች አትሌቲክስ ሻምፒዮና በሐዋሳ ይካሄዳል - ኢዜአ አማርኛ
12ተኛው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች አትሌቲክስ ሻምፒዮና በሐዋሳ ይካሄዳል
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 21/2016(ኢዜአ)፡- 12ተኛው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች አትሌቲክስ ሻምፒዮና በሐዋሳ ከተማ እንደሚካሄድ ተገለፀ።
ውድድሩ ከሰኔ 25 እስከ 29 ቀን 2016 ዓ.ም እንደሚከናወን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ገልጿል።
በውድድሩ አጠቃላይ 971 አትሌቶች በተለያዩ የሜዳ ላይ ተግባራት ውድድር ይሳታፋሉ።
የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ የቴክኒክ ክፍል ኃላፊ አስፋው ዳኜ፤ የውድድሩ ዋና ዓላማ ተተኪ አትሌቶች ለማፍራትና፤ በሀገሪቱ ላሉ አትሌቶች የውድድር ዕድል ለመፍጠር መሆኑን ገልፀዋል።
ሚኒማ የሚያሟሉና ጥሩ ውጤት የሚያስመዘግቡ ተወዳዳሪዎችም፤ ነሓሴ ላይ በፔሩ ሊማ ከተማ ለሚደረገው የዓለም ከ20 ዓመት በታች ውድድር ላይ ሀገራቸውን ወክለው ይሳተፋሉ ብለዋል።
የዕድሜ ተገቢነትን በተመለከተም ተወዳዳሪዎች ዕድሜን በሚመጥን መልኩ እንዲሳተፉ ለክልል ተቋማት አቅጣጫ ቢቀመጥላቸውም፤ በታሰበው ደረጃ ባለመሳካቱ ፌዴሬሽኑ ወደ ምርመራ መግባቱን ነው የገለፁት።
ከውድድሩም በፊት የዕድሜ ተገቢነትን ለማረጋገጥ የኤም አር አይ ምርመራ እንደሚያደረግና ተምርምረው የሚያልፉ ተወዳዳሪዎች ብቻ በውድድሩ እንደሚሳተፉ ተናግረዋል።
ከዕድሜ እርከኑ በላይ ሆኖ ውድድሩን ለመሳተፍ በመጣ ተወዳዳሪ ላይ ግን፤ የማያዳግም እርምጃ ፌዴሬሽኑ እንደሚወሰድ ነው የገለፁት።
በሌላ በኩል 40ኛው የሻምበል አበበ ቢቂላ ማራቶን ውድድር፤ በሐዋሳ ከተማ ሰኔ 30 /2016 ዓ.ም እንደሚከናወን ተገልጿል።
ለውድድሩም ሽልማት ከ3 ነጥብ 8 ሚሊየን ብር በላይ እንደተዘጋጀ፤ ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።