በ23ተኛው የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ለተካፈለው የአትሌቲክስ ልዑክ ቡድን እውቅናና ሽልማት ተሰጠ - ኢዜአ አማርኛ
በ23ተኛው የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ለተካፈለው የአትሌቲክስ ልዑክ ቡድን እውቅናና ሽልማት ተሰጠ
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 21/2016(ኢዜአ)፡-በ23ተኛው የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ለተካፈለው የአትሌቲክስ ልዑክ ቡድን የአንድ ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ብር ሽልማት ተበርክቷል።
በዕውቅና መርኃ ግብሩ ወርቅ ላመጡ አትሌቶች የ40 ሺህ፣ብር ላመጡ የ25 ሺህ ብር፣ ነሐስ ላመጡ የ15 ሺህ፤ እንዲሁም ዲፕሎማ ላመጡ የ10 ሺህ ብር ሽልማት በሁለቱም ፆታዎች ተበርክቶላቸዋል።
ለአሰልጣኞች፣ የቡድን መሪዎች፣ ኦፊሻሎች፣ ሐኪሞች፣ ፊዚዮቴራፒስቶች ሽልማት የተሰጠ ሲሆን ፌዴሬሽኑ አጠቃላይ ለሽልማት አንድ ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ብር ወጪ አድርጓል።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ በዚሁ ጊዜ እንደገለጸችው፤ የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ለብዙ ውድድሮች መነሻ ነው።
በዚህ ውድድር አትሌቶች ውጤት ማምጣታቸው ለነገ ስኬታማ የአትሌቲክስ ጉዟቸው ትልቅ መንገድ እንደሚከፍት ገልፀዋል።
ስለሆነም ይህን መነሻ አድርገው ራሳቸውን ከወዲሁ እንደ ኦሎምፒክ ላሉት ውድድሮች ማዘጋጀት አለባቸው ብለዋል።
በ23 ተኛው የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና የቡድን መሪ የነበሩት ፎዚያ ኢድሪስ በበኩላቸው አትሌቶች የተለያዩ መሰናክሎችን በማለፍ ሀገራቸውን ወክለው መልካም ውጤት አምጥተዋል ብለዋል።
በተለይ በካሜሮን የነበረው ሙቀት፤ እንዲሁም ከማረፊያና ከሆቴል ጋር በተያያዘ ያጋጠሙ ችግሮችን በመቋቋም አትሌቶች ሜዳሊያዎችን ይዘው እንደመጡ ገልፀዋል።
በአሥር ሺህ ሜትር ወርቅ፤ በአምስት ሺህ ሜትር ደግሞ ብር ያመጣው አትሌት ንብረት መላክና በእርምጃ ውድድር የወርቅ ሜዳሊያ ያመጣችው ስንታየሁ ማስሬም ከባድ ሙቀት ተቋቁመው እንዳሸነፉ ተናግረዋል።
በ23ኛው የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ በ5 ወርቅ፣ በ4 ብር እና በአንድ ነሐስ በአጠቃላይ በ10 ሜዳልያዎች ደቡብ አፍሪካ፣ ኬንያንና ናይጄሪያን ተከትላ 4ኛ ደረጃን በመያዝ ውድድሩን አጠናቃለች።