ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል የምትጫወተው ሚና ለቀጣናው ሰላምና መረጋጋት ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው - ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል የምትጫወተው ሚና ለቀጣናው ሰላምና መረጋጋት ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው - ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 21/2016(ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል የምትጫወተው ሚና ለቀጣናው ሰላምና መረጋጋት ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ መሆኑን የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ ገለጹ።
የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርኑ ጁላ በቢሸፍቱ የሚገኘውን የምስራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል ሞተራይዝድ ሻለቃ ጠቅላይ ጦር ሰፈር ጎብኝተዋል።
ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ የምስራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ሰላም ያላትን ጉልህ ሚናና ቁርጠኝነት የሚያሳይ መሆኑን ገልፀዋል።
ኢትዮጵያ የምስራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል እንዲመሰረት ቀዳሚ ሀሳብ አመንጭና ግንባር ቀደም ተዋናይ መሆኗን ገልፀዋል።
በዕለቱ የተመለከቱት ለግዳጅ ዝግጅ የሆነ ኃይልም ኢትዮጵያ የቀጣናው አለኝታ መሆኗን ያረጋገጠ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል የምትጫወተው ሚና ለቀጣናው ሰላምና መረጋጋት ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ መሆኑንም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ለምስራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል የምታዋጣው ኃይል በዓለም አቀፍ መስፈርት መሰረት የተገነባ ዝግጁ ሰራዊት መሆኑን ገልፀዋል።
ሰራዊቱ እንደ ስሙ በተሰማራበት መስክ ሁሉ ተልዕኮውን ለመወጣት የሚያስችል ሙሉ ዝግጁነት ያለው መሆኑን መመልከታቸውን ጠቅሰው ለዚህም ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከቱ የመከላከያ እና የፌዴራል ፖሊስ አመራሮችን አድንቀዋል።
ሰራዊቱ የኢትዮጵያን ገፅታ ሙሉ የሚያደርግ እና ለቀጣናው ሰላምና መረጋጋት በቁርጠኝነት የሚሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
ተጠባባቂ ኃይሉ ሁልጊዜም ለተልዕኮ ዝግጁ መሆኑን ገልፀው፤ ኢትዮጵያ ለምስራቅ አፍሪካ ሰላምና ደህንነት መረጋገጥ የምታደርገውን ተግባራዊ እንቅስቃሴ አጠናክራ እንደምትቀጥል ተናግረዋል።