በ17ኛው የአውሮፓ ዋንጫ እነማን ብዙ ለጎል የሚሆኑ ኳሶችን አቀበሉ? 

በእግር ኳስ ጨዋታ ከግብ አስቆጣሪዎች ጀርባ ኳስን ፍትፍት አርገው ጨርሰው የሚያቀብሉ ተጫዋቾች አሉ።

አንድ ተጫዋች ግብ ሲያገባ ከማግባቱ ባልተናነሰ ማን ኳሱን አቀበለው? የሚለው ጥያቄ በተመልካቾች ይነሳል።

በእግር ኳስ እድገት ውስጥ በተለይም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ለጎል ኳስ አመቻችተው የሚያቀብሉ ተጫዋቾች ትልቅ ዋጋ ይሰጣቸዋል። 

በጀርመን አስተናጋጅነት እየተካሄደ በሚገኘው 17ኛው የአውሮፓ ዋንጫ የምድብ ጨዋታዎች ወደ ጥሎ ማለፉ ተሸጋግረዋል።

ወደ ሩብ ፍጻሜ የሚገቡ ሀገራትን የሚለዩ የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች ከነገ ጀምሮ ይካሄዳሉ።

ከሰኔ 7 እስከ 19 ቀን 2016 ዓ.ም በተደረጉ የአውሮፓ ዋንጫ 36 የምድብ ጨዋታዎች 81 ግቦች ከመረብ ላይ አርፈዋል።

ከተቆጠሩት ግቦች ውስጥ አብዛኛውን እነማን አቀበሉ? የሚለውን በዚህ ጽሁፍ ይዘን ቀርበናል።

አራት ተጫዋቾች እስከ አሁን በውድድሩ በተመሳሳይ ሁለት ግቦችን ለግብ አመቻችተው አቀብለዋል።

አጓጊ ፉክክር በተደረገበት ምድብ 5 ሮማንያ 4 ነጥብ በመያዝ ምድቡን በበላይነት አጠናቃ ወደ ጥሎ ማለፉ ገብታለች። ቡድኑ በጨዋታዎቹ 4 ግቦችን ከመረብ ላይ አሳርፏል።

ሮማንያ ካስቆጠረቻቸው 4 ግቦች 2ቱን ለግብ አመቻችቶ ያቀበለው የ25 ዓመቱ የፓርማ የክንፍ ተጫዋች ዴኒስ ማን ነው። 

ማን ኳሶቹን አመቻችቶ ያቀበለው ሮማንያ ዩክሬንን 3 ለ 0 ባሸነፈችበት ጨዋታ ነው።

የክንፍ መስመር ተጫዋቹ በዘንድሮው የአውሮፓ ዋንጫ የተጋጣሚ ተከላካዮችን በፍጥነት ኳስን በማንከባለል ፋታ እየነሱ ካሉ ተጫዋቾች መካከል ይገኝበታል።

በተመሳሳይ በምድብ 5 ስሎቫኪያ በ4 ነጥብ ምርጥ ሶስተኛ ሆና ጥሎ ማለፉን መቀላቀሏ የሚታወስ ነው።

ስሎቫኪያ በሶስቱ የምድብ ጨዋታዎች ሶስት ግቦችን አስቆጥራለች። ከነዚህም ውስጥ ሁለቱን ለግብ አመቻችቶ ያቀበለው ለሀገሩ ክለብ ስሎቫን ብራቲስላቫ የሚጫወተው ጁራጅ ኩችካ ነው።

ኩችካ ስሎቫኪያ ቤልጂየምን 1 ለ 0 ባሸነፈችበትና ከሮማንያ አንድ አቻ በተለያየችበት ጨዋታ ኳሶቹን አመቻችቶ አቀብሏል። 

በምድብ 1 በ5 ነጥብ 2ኛ ደረጃን ይዛ በመጨረስ 2ኛ ደረጃን ይዛ ያለፈቸው ስዊዘርላንድ በሶስቱ ጨዋታዎች 5 ግቦችን አስቆጥራለች።

ከኖቲንግሃም ፎረስት በውሰት ለቦሎኛ የሚጫወተው የ32 ዓመቱ አማካይ ሬሞ ፍሩለር ስዊዘርላንድ ሀንጋሪን 3 ለ 1 ስታሸንፍ እንዲሁም ከጀርመን አንድ አቻ ስትለያይ ለሁለቱ ግቦች መቆጠር የተጫዋቹ እጅ አለበት።

ከዚሁ ጋር በተገናኘም ስዊዘርላንድ ሀንጋሪን ባሸነፈችበት ተጫዋች ማርክ ኤቢሸር በጨዋታው ግብ በማስቆጠርና ለግብ የሚሆን ኳስ አመቻችቶ አቀብሏል።

ይህም ኤቢሸርን በውድድሩ ታሪክ በአንድ ጨዋታ ጎል ያገባና ለግብ የሚሆን ኳስን አመቻችቶ ያቀበለ የመጀመሪያው ስዊዘርላንዳዊ ተጫዋች አድርጎታል።

"የሞት ምድብ" በተባለው ምድብ 2 ክሮሺያ 2 ነጥብ ይዛ ሶስተኛ ደረጃን ይዛ በማጠናቀቅ ከውድድሩ ውጪ መሆኗ ይታወቃል።

የ32 ዓመቱ የኦሳሱና አጥቂ አንት ቡዲሚር ክሮሺያ በውድድሩ ተሳትፎ ካስቆጠረቻቸው 3 ግቦች 2ቱን ለግብ አመቻችቶ አቀብሏል።

ቡዲሚር ኳሱን አመቻችቶ ያቀበለው ክሮሺያ ከአልባኒያ ሁለት እኩል እንዲሁም ከጣልያን ጋር ድራማዊና ልብ አንጠልጣይ በሆነ ሁኔታ አንድ አቻ በተለያየችበት ጨዋታዎች ላይ ነው።

በተያያዘም ምድብ 2 ስፔን ክሮሺያን 3 ለ 0 ባሸነፈችበት ጨዋታ ታዳጊው ስፔናዊ ላሚን ያማል በ16 ዓመት በ338 ቀናት ዳኒ ካርቫያል ያስቆጠረውን ግብ አመቻችቶ በመቀበል በውድድሩ ታሪክ በትንሽ እድሜው ለጎል የሚሆን ኳስ የሰጠ ተጫዋች የሚል ክብረ ወሰንን ጨብጧል።

ያማል በዚህ ጨዋታ በአውሮፓ ዋንጫ ላይ የተሰለፈ በእድሜ ትንሹ ተጫዋች ክብረ ወሰንንም ሰብሯል።

በተጨማሪም በአውሮፓ ዋንጫው በሶስት ግቦች የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን እየመራ የሚገኘው የጆርጂያው አጥቂ ጆርጄስ ሚካውታድዛ ካገባቸው ግቦች በተጨማሪ አንድ ለግብ የሚሆን ኳስ አመቻችቶ አቀብሏል።

የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር በዘንድሮው የአውሮፓ ዋንጫ ማን ብዙ ለጎል የሚሆን ኳስ አቀበለ? ለሚለው ጉዳይ ትልቅ ግምት ሰጥቶታል።

ማህበሩ በውድድሩ ሁለትና ከዚህ በላይ ተጫዋቾች በተመሳሳይ የግብ መጠን የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ሆነው ቢያጠናቅቁ አንደኛ የሚወጣውን የሚለየው ከተጫዋቾቹ ማን የተሻለ ለግብ የሚሆን ኳስ አቀበለ? በሚለው መስፈርት ነው።

የ17ኛው የአውሮፓ ዋንጫ እስከ ሐምሌ 7 ቀን 2017 ዓ.ም የሚቆይ ሲሆን የግብ አግቢዎችና የኳስ አቀባዮቹ ፉክክር በያዘው ግለት ይቀጥላል ተብሎ ይጠበቃል።

 

 

 

 

 

 

 

    

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም