የዓለም ጂሞሎጂስት ፋውንዴሽን በከበሩ ድንጋዮችና ጌጣጌጦች ልየታና ቆረጣ ዘርፍ ያሰለጠናቸውን ባለሙያዎች አስመረቀ - ኢዜአ አማርኛ
የዓለም ጂሞሎጂስት ፋውንዴሽን በከበሩ ድንጋዮችና ጌጣጌጦች ልየታና ቆረጣ ዘርፍ ያሰለጠናቸውን ባለሙያዎች አስመረቀ
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 20/2016(ኢዜአ)፦ የዓለም ጂሞሎጂስት ፋውንዴሽን በከበሩ ድንጋዮችና ጌጣጌጦች ልየታና ቆረጣ ዘርፍ ያሰለጠናቸውን ጂሞሎጂስቶች አስመረቀ።
ሥልጠናው ለ11 ተከታታይ ወራት ሲሰጥ መቆየቱ ተገልጿል።
የማዕድን ሚኒስትሩ ኢንጂነር ኃብታሙ ተገኝ በዚሁ ጊዜ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ተመራቂዎች የኢትዮጵያን የከበሩ ማዕድናት ዘርፍ ወደ ቀጣይ ምዕራፍ የምታሸጋግሩ ናችሁ ብለዋል።
ኢትዮጵያ ከ40 በላይ የከበሩ የማዕድን ዓይነቶች ቢኖሯትም እስካሁን ድረስ በአግባቡ ለይቶ ጥቅም ላይ በማዋል ረገድ ውስንነቶች መኖራቸውን ገልፀዋል።
የከበሩ ድንጋዮች ምንነት የሚለየውና ዋጋቸው የሚተመነው ከውጭ በመጣ አካል መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህም ኢትዮጵያ ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም እንዳታገኝ አድርጓት ቆይቷል ብለዋል።
ሚኒስቴሩ ይህን ችግር በዘላቂነት የሚቀይር የሪፎርም ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝና የዓለም ጂሞሎጂስት ፋውንዴሽን ያስመረቃቸው ተመራቂዎች ይህን ተግባር ለማገዝ ሚናቸው የጎላ መሆኑን አመላክተዋል።
ዛሬ የተመረቁ ሰልጣኞች ኢትዮጵያ ለዓለም ገበያ ተወዳዳሪ የሆኑ የከበሩ ማዕድናትን እንድታቀርብ ትልቅ አደራ ተጥሎባቸዋል ብለዋል።
የዓለም ጂሞሎጂስት ፋውንዴሽን ፕሮጀክት የአፍሪካ ዳይሬክተር ኃይማኖት ሲሳይ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ያላትን የማዕድን ኃብት በአግባቡ በመለየት ጥቅም ላይ ለማዋል መጀመሪያ በዘርፉ ብቁ የሰው ኃይል ማፍራት እንደሚገባ አመላክተዋል።
የዓለም ጂሞሎጂስት ፋውንዴሽን ፕሮጀክት አፍሪካ ባለፉት 11 ወራት በምስራቅ አፍሪካ የመጀመሪያ የሆኑትን የጂሞሎጂስት ሠልጣኞችን ለምረቃ አብቅቷል ብለዋል።
ፋውንዴሽኑ አሁን ላይ በከበሩ ድንጋይ ልየታ መስክ 12 ባለሙያዎችን በማፍራት ለዘርፉ እድገት የበኩሉን እየተወጣ እንደሚገኝና በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
ከሠልጣኞች መካከል ሔኖክ ግርማ፣ ታምራት መኮንን እና ቁምላቸው ተስፋዬ፤ የሥልጠናው ዕድሉ ተጠቃሚ በመሆናቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልፀዋል።
በቀጣይ በሰለጠኑበት ዘርፍ ከራሳቸው አልፈው አገራቸውን ለማገልገል ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
ጂሞሎጂ የከበሩ ማዕድናትንና ጌጣጌጦችን የሚለይ፣ የሚያጠና፣ የሚቆርጥና እሴት መጨመር ላይ የሚያጠና ሳይንስ ነው።