በክልሉ ጭስ አልባ ትራንስፖርትን በማስፋፋት የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋምና የነዳጅ ፍጆታን ለመቀነስ ትኩረት ተሰጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ጭስ አልባ ትራንስፖርትን በማስፋፋት የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋምና የነዳጅ ፍጆታን ለመቀነስ ትኩረት ተሰጥቷል
ሐዋሳ ፤ ሰኔ 20/2016 (ኢዜአ)፡- በሲዳማ ክልል ጭስ አልባ ትራንስፖርትን በማስፋፋት የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋምና የነዳጅ ፍጆታን ለመቀነስ ትኩረት መሰጠቱን የክልሉ መንገድ ልማትና ትራንስፖርት ቢሮ አስታወቀ፡፡
ቢሮው ከሮያል ቢዝነስ ግሩፕና ሚኢአና ኮንስትራክሽንና ማኑፋክቸሪንግ ጋር በመተባበር ጭስ አልባ የሆነውን የቤላ ኢ ሞተርስ ኤሌክትሪክ ተሸከርካሪ ማስተዋወቂያ መድረክ በሃዋሳ አካሂዷል፡፡
የቢሮ ሃላፊው አቶ ታምሩ ታፌ በወቅቱ እንደገለጹት የትራንስፖርት ዘርፉን በአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች በማገዝ ወቅቱ የሚጠይቀውን አገልግሎት መስጠት ያስፈልጋል፡፡
የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ተሸከሪካሪዎች በነዳጅ ሃይል የሚንቀሳቀሱ በመሆናቸው ከፍተኛ የገንዘብ ወጪ ከመጠየቃቸው ባለፈ ለአካባቢ ብክለትና ለጤና ተግዳሮት እየሆኑ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በመሆኑም በክልሉ ጭስ አልባ ትራንስፖርትን በማስፋፋት የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋምና ለነዳጅ የሚወጣውን ፍጆታ ለመቀነስ ትኩረት መሰጠቱን ገልጸዋል፡፡
ዛሬ የተዋወቁት ጭስ አልባ ባለሶስት እግር የኤሌክትሪክ ተሸከሪካሪዎችን በሃዋሳና በክልሉ የተለያዩ ከተሞች በማስፋፋት በሂደት ከነዳጅ ተሸካሪካሪዎች ነጻ የማድረግ የመንግስት ፖሊሲን ተግባራዊ የማድረግ ስራ ይሰራል ብለዋል፡፡
በዚህም ምርታማናጤንነቱ የተጠበቀ ትውልድ በማፍራት የሚፈለገውን የብልጽግና ጉዞ ማረጋገጥ እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡
ጭስ አልባ የኤሌክትሪክ ተሸሪካሪዎች የሚሰጡትን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ በመረዳት በዘርፉ የተሰማሩ ማህበራትና ተቋማት ለስራው ውጤታማነት የበኩላቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡
የቤላ ኢ ሞተርስ ስራ አስኪጅ አቶ ሳምሶን ኢዮብ በበኩላቸው ጭስ አልባ ተሸሪካሪዎቹ ከ90 ከመቶ በላይ በሃገር ውስጥ የተገጣጠሙ በመሆናቸው የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ አካል ናቸው ብለዋል፡፡
መንግስት ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚን ለመገንባት የሚያደርገውን ጥረት በማገዝ ጭስ አልባ የኤሌክትሪክ ተሸከሪካሪዎችን ወደ መገጣጠም መግባታቸውን ተናግረዋል፡፡
ተሸከርካሪዎቹ በኤክትሪክ ቻርጅ የሚደረጉና በሶላር የሚሰሩ እንዲሁም አማራጭ ኢነርጂን መጠቀም የሚያስችል ሲስተም የተገጠመላቸው መሆናቸው ልዩ ያደርጋቸዋል ብለዋል፡፡
በቀጣይም በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ብስክሌቶችንና ባለአራት እግር ተሸከርካሪዎችን ለመገጣጠም እቅድ ይዘው እየሰሩ መሆኑን አስታውቀዋል።
በመድረኩ በጭስ አልባ የኤልሌክትሪክ ተሸከርካሪዎች ጠቀሜታና አስፈላጊነት ላይ ያተኮረ ውይይት የተደረገ ሲሆን ተሸሪካሪዎቹም ለእይታ ቀርበዋል፤በትራንፖርት ዘርፍ የተሰማሩ ማህበራትና ባለድርሻ አካለትም ተሳትፈዋል፡፡