የኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት የሁለት ተቋማትን ሰነዶች የማስወገድ ስራ መጀመሩን አስታወቀ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት የሁለት ተቋማትን ሰነዶች የማስወገድ ስራ መጀመሩን አስታወቀ
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 20/2016 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት የፌደራል ዋና ኦዲት መስሪያ ቤትና የሙገር ሲሚንቶ ሰነዶችን የማስወገድ ስራ መጀመሩን አስታወቀ።
ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት በአዋጅ ቁጥር 179/91 ጥቅም ላይ የማይውሉ የተቋማትን ሰነዶች የማስወገድ ተግባር እና ኃላፊነት ተሰጥቶታል።
በዚህም አገልግሎቱ በአንቀጽ 15(1እና3) ሰነድ አመንጪ ተቋማት በራሳቸው ሰነድ ማስወገድ እንደማይችሉና ተቋሙ የዚህ ኃላፊነትና ስልጣን እንደተሰጠው በመገንዘብ በኬሚካል ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን የሙገር ሲሚንቶ ፋብሪካ እና የፌዴራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ከእንቅስቃሴ ውጪ የሆኑ ሰነዶችን አስፈላጊው ሙያዊ፣ ህጋዊና ተቋማዊ አሰራርን ተከትሎ ዛሬ የውገዳ ማስጀመሪያ ስነ ስርዓቱን አከናውኗል።
በስነ ስርዓቱ ላይ የተገኙት የብሄራዊ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ይኩኖአምላክ መዝገቡ እንደገለጹት ተቋሙ በተሰጠው ስልጣን መሰረት በተደራጀ መልኩ የሰነድ አመንጪ ተቋማት ሰነዶችን ያስወግዳል።
አቶ ይኩኖአምላክ መዝገቡ የዛሬው ሁነት ላይ ከመድረስ በፊት አዋጁ በተግባር እንዲውል ሀገራዊ የሆነውን የኢትዮጵያ የሰነድ አስወጋጅ ኮሚቴ ከማቋቋም ጀምሮ ብዙ ሂደት የሚሹ ስራዎች መከናወናቸውን ተናግርዋል።
በዚህም ሁለቱ ተቋማት ለታሪክ የሚቀመጠው ተለይቶ የሚወገደው በህጋዊ መልኩ ተጣርቶ የሚፈጸምበትን መንገድ በመምረጥ ወደ ተቋሙ በመምጣታቸው አመሠግነው ሌሎች ተቋማትም ይህንኑ መንገድ እንዲከተሉና በራሳቸው ሰነዶችን አስወግደው በተቋሙ በህግ አግባብ ከመጠየቅ እንዲድኑ በአፅንኦት ገልጸዋል።
የህጋዊ ሰነድ ውገዳ ኮሚቴ ስብሳቢና የተቋሙ የአብያተ መዛግብትና አብያተ መጻሕፍት መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ መኮንን ከፋለ በበኩላቸው ስራው በከፍተኛ ጥንቃቄና ሙያዊ ስነምግባርን ተከትሎ እንደሚሰራ ገልጸዋል።
የሰነዱ አመንጪ በሆኑት ሁለቱ ተቋማት እና በተቋሙ ባለሙያዎች በተናጠልና በጋራ በተለያየ ዙር ሙያዊ ስራ ተሰርቶ ከሚወገዱት ሰነዶች፤ ከፌዴራል ዋና ኦዲተር መስሪያቤት ከ5600 ፋይል ተወጋጅ ሰነዶች 214 እንዲሁም በኬሚካል ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን የሙገር ሲሚንቶ ፋብሪካ 700 ፋይል ተወጋጅ ሰነዶች 136 መዛግብት የሚሆኑ መለየታቸውን ጠቁመዋል።
የሰነዱ አመንጪ የሆኑት ተቋማት ተወካዮች ወይዘሮ ዘነበች እና አቶ መሀመድ ኢብራሂም ጠቀሜታ የሌላቸው ሰነዶች ክምችት የሚፈጥሩባቸውን የስራ መስተጓጎል ስለተቀረፈላቸው ለዚህም ተቋሙ አስፈላጊውን ሙያዊ እገዛና ድጋፍ ስላደረገላቸው ምስጋናቸውን ገልፀዋል።