ከተረጂነት ለመውጣት የተጀመረውን ሀገራዊ ግብ ለማሳካት ያለብንን ድርብ ኃላፊነት በአግባቡ ለመወጣት ዝግጁ ነን - የኢዜአ አመራርና ሠራተኞች - ኢዜአ አማርኛ
ከተረጂነት ለመውጣት የተጀመረውን ሀገራዊ ግብ ለማሳካት ያለብንን ድርብ ኃላፊነት በአግባቡ ለመወጣት ዝግጁ ነን - የኢዜአ አመራርና ሠራተኞች
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 20/2016(ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያን ከተረጂነት ለማላቀቅ የተጀመረውን ሀገራዊ ግብ እንዲሳካ የሚጠበቅባቸውን ድርብ ኃላፊነት በአግባቡ ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት አመራሮችና ሠራተኞች ገለጹ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት አመራሮችና ሠራተኞች "ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለተሟላ አገራዊ ክብር፣ ነፃነትና ሉዓላዊነት" በሚል መሪ ኃሳብ ውይይት አካሂደዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሰይፈ ደርቤ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ሀገሪቱ ከተረጂነት አስተሳሰብ ለመላቀቅ የጀመረችውን ግብ ተገንዝበው ለሌሎች ማስረዳትና ማሳወቅ ይጠበቅባቸዋል።
ኢትዮጵያ ከተረጂነት አስተሳሰብ በመላቀቅ የልማትና የብልጽግና ጉዞዋን ማሳካት የሚያስችል ተግባራዊ እንቅስቃሴ ላይ ትገኛለችም ብለዋል።
ተረጂነት ኢትዮጵያ የጀመረቻቸውን የመፍጠር፣ የመለወጥና ከችግር የመላቀቅ ግብን የሚገታ አስተሳሰብ መሆኑንም ገልፀዋል።
ተረጂነት ለኢትዮጵያ የማይመጥን ክብረ-ነክ ተግባር ነው ሲባል ኢትዮጵያ ለትምህርት፣ ለጤናና ሌሎች መሠረተ-ልማቶች ከለጋሽ አካላት ድጋፍ አያስፈልጋትም ማለት አይደለም ብለዋል።
በመሆኑም የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ይሄንን በውል ተረድተው የዜጎችን የተረጅነት አስተሳሰብ መቀየር የሚያስችል አጀንዳ መቅረጽና ማስረጽ ይገባቸዋል ብለዋል።
ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ኃብቶቿን የማልማት ጅምሮቿን አጠናክራ መቀጠል እንድትችል የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ገልፀዋል።
የመነሻ ጽሑፍ ያቀረቡት የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ነጋሲ አምባዬ፤ በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ከተረጂነት አስተሳሰብ መላቀቅ ይገባል ብለዋል።
ኢትዮጵያ የሚለማ የተፈጥሮ ጸጋ፣ ሰርቶ መለወጥ የሚችል የሰው ኃይል እያላት በተረጅነት አስተሳሰብ መኖርን ክብርን የሚያሳጣ ለእኛም የማይመጥን ነው ብለዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት የተጀመሩት የበጋ መስኖ ስንዴ፣ የሌማት ትሩፋት፣ አረንጓዴ አሻራና መሰል እሳቤዎች በራሳችን አቅም ከተመጽዋችነት መውጣት እንደምንችል ማሳያዎች መሆናቸውን ገልፀዋል።
በመሆኑም ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የተጀመሩ ተግባራትን በማጠናከር በተቀናጀ የልማት እንቅስቃሴ ተረጂነትን ከነአስተሳሰቡ ማስወገድ ይገባል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ያሏትን እምቅ ኃብቶችና ጸጋዎች በመጠቀም ከተረጂነት አስተሳሰብ መላቀቅ የምትችልበት ደረጃ ላይ መድረሷን የገለጹት ደግሞ የውይይቱ ተሳታፊዎች ናቸው።
ባለፉት የለውጥ ዓመታት በሁሉም ዘርፎች የተመዘገቡት ስኬቶች በአጭር ጊዜ ከተረጂነት መላቀቅ እንደሚቻል አመላካች መሆናቸውን ገልፀዋል።
ለአደጋ ሥጋት የማይበገር የሰብዓዊ ድጋፍ ሥርዓት ለመዘርጋት የተጀመረው ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ በማጎልበት መልማት የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎችን ተጠቅሞ ከተረጂነት መላቀቅ ይገባልም ነው ያሉት።
ኢትዮጵያውያን ባላቸው ጸጋ ሰርተው መለወጥና ከተረጅነት መውጣት እንደሚችሉ ማንቃትና ማስገንዘብ ሙያዊ ኃላፊነታቸው መሆኑን ገልፀዋል።
የተረጂነት አስተሳሰብን ለማስወገድ የተጀመረውን አገራዊ ጥረት ከግብ ለማድረስ መገናኛ ብዙኃን ድርብ ኃላፊነት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።
በመሆኑም ኢትዮጵያን ከተረጂነት አስተሳሰብ ወደ ምርታማነት መቀየር የሚያስችል የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ሥራ እናከናውናለን ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ተፈራ በቀለ፤ ከተረጂነት ለመላቀቅ የመንግሥት ትልቁ ትኩረት ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ መሆኑን ገልፀዋል።
ለዚህ ደግሞ በአንድ አካባቢ ያለውን የምርታማነት ተሞክሮ ወደ ሌሎች አካባቢዎች በማስፋት ውጤታማ ሥራዎችን ማስፋት እንደሚገባ ነው ያስገነዘቡት።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሰይፈ ደርቤ፤ ኢዜአ ብሔራዊ መግባባትን መፍጠር የሚችሉ አጀንዳዎችን በማስረጽ የተሰጠውን አገራዊ ተልዕኮ በብቃት ይወጣል ብለዋል።
የተረጂነት አስተሳሰብ ድህነትን በማስፋፋት ለብሔራዊ መግባባት ፀር መሆኑን ገልጸው፤ ኢትዮጵያውያን ከዚህ አስተሳሰብ እንዲላቀቁ በትጋት ይሰራል ብለዋል።