ቀጥታ፡

ሕብረተሰቡ የትምህርት ተቋማትን ለማሻሻል የተጀመሩ ሥራዎችን ለመደገፍ የሚያበረክተውን አስተዋፅዖ እንዲያጠናክር ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 20/2016(ኢዜአ)፦ሕብረተሰቡ መንግሥት በኢትዮጵያ የትምህርት ተቋማትን ለማሻሻል የጀመራቸውን ሥራዎች ለመደገፍ እያበረከተ ያለውን አስተዋፅዖ አጠናክሮ እንዲቀጥል የትምህርት ሚኒስቴር ጥሪ አቀረበ። 

የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር 11ኛውን የትምህርት ጥራት ኮንፍረንስ እንዲሁም "የሕዝብ ፈንድ ለትምህርት" ዘመቻን ዛሬ በይፋ አስጀምሯል።


 

በመርኃ-ግብሩ የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ አየለች እሸቴን ጨምሮ ሌሎች በትምህርት ዘርፉ የሚሰሩ ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ አየለች እሸቴ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ሀገራት የደረሱበት የእድገት ደረጃ ለማድረስ ትውልዱን ጥራት ባለው የትምህርት ሥርዓት እንዲያልፍ ማድረግ ይጠበቅብናል።

የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በርካታ የቤት ሥራዎች እንዳሉ በመግለጽ ከዚህ ውስጥ አንዱ የትምህርት ተቋማትን ለመማር ማስተማር ምቹ ማድረግ መሆኑን አንስተዋል።

ሀገር አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ትምህርት ቤቶች እንዲኖሩ ለማስቻል መንግሥት ሕብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ በ2015 ዓ.ም ትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ ማስጀመሩን አስታውሰዋል። 

በትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ ከ 25 ቢሊየን ብር በላይ ኃብት በማሰባሰብ በርካታ ትምህርት ቤቶችን ደረጃ የማሻሻል፣ አዲስ የመገንባትና ግብዓቶችን የማሟላት ሥራ መሠራቱን ገልፀዋል።

ይህም እንቅስቃሴ ውጤታማ እንዲሆን የትምህርት ማኅበረሰቡና ሌሎች አካላት ተሳትፎ የላቀ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ሕብረተሰቡም መንግሥት በኢትዮጵያ የትምህርት ተቋማትን ለማሻሻል የጀመራቸውን ሥራዎች ለመደገፍ እያበረከተ ያለውን አስተዋፅዖ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር ፕሬዝዳንት ዮሐንስ በንቲ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ማኅበሩ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ መምህራን ግንባር ቀደም ተሳታፊ ሆነው ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።


 

በኮንፍረንሱ የትምህርት ጥራትን ማሻሻል በሚያስችሉ አጀንዳዎች ላይ ምክክር መደረጉንና ትምህርት ለትውልድ ንቅናቄን የሚደግፍ "የሕዝብ ፈንድ ለትምህርት" ዘመቻ አስጀምሯል ብለዋል።

የዚህም ዋና ዓላማ ሕብረተሰቡ ባለኃብቶችና የተለያዩ ተቋማቶች ትምህርት ቤቶች የማሻሻል ሥራ ላይ በንቃት እንዲሳተፍ የማንቃት ሥራ ለመሥራት መሆኑን ገልጸዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም