ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ አስተዳደራዊ ፍርድ ቤት ወደ ሥራ ለመግባት የሚያስችሉ የዝግጅት ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን ገለጸ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 20/2016(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ አስተዳደራዊ ፍርድ ቤት ወደ ሥራ ለመግባት የሚያስችሉ የዝግጅት ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን የፍርድ ቤቱ ሰብሳቢ ዳኛ አቶ አብነት ዘርፉ ገለጹ። 

የካፒታል ገበያ ቀልጣፋ የፋይናንስ አሠራር፣ የተሻለ የቁጠባ አቅም፣ ሰፊ የኢንቨስትመንት ዕድልና ፍትሃዊ የኃብት ክፍፍል የሚፈጥር ነው።

ይህንንም ከግምት በማስገባት በኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ በአዋጅ ቁጥር 1248/2013 ተቋቁሟል። 

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ አስተዳደራዊ ፍርድ ቤት ሰብሳቢ ዳኛ አብነት ዘርፉ የካፒታል ገበያ ማክሮ ኢኮኖሚው እንዲረጋጋና ጤናማ የካፒታል ፍሰት እንዲኖር ያደርጋል ብለዋል።

ሰዎች ኃብታቸውን በቀላሉ ኢንቨስት እንዲያደርጉ እንዲሁም የውጭ መዋዕለ-ንዋዮች ወደ ሀገር እንዲገቡ የሚያደርግና ከዓለም ጋር የሚያስተሳስር ድልድይ መሆኑን ተናግረዋል።

ሥርዓቱ በርካታ አካላት የሚሳተፉበት መሆኑን ገልጸው፤ በዚህ ውስጥ ቅሬታና አቤቱታ ያላቸው ተዋናዮች ቅሬታቸውን የሚያቀርቡበት የካፒታል ገበያ አስተዳደራዊ ፍርድ ቤት በመንግሥት በአዋጅ መቋቋሙን ገልፀዋል።

ፍርድ ቤቱ በዋናነት በመዋዕለ-ንዋይ ግብይት ወቅት የካፒታል ገበያ ባለሥልጣን የሚሰጣቸው ውሳኔዎች ላይ ቅሬታ ያላቸው አካላት የሚያቀርቡትን ቅሬታ መርምሮ ውሳኔ የሚሰጥ መሆኑን ተናግረዋል።

ፍርድ ቤቱ አሁን ላይ የዝግጅት ሥራዎችን በማጠናቀቅ ሂደት ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

የካፒታል ገበያ አስተዳደራዊ ፍርድ ቤት ለሚቀርቡ ቅሬታዎች በቀላል እና አነስተኛ ወጪ መፍትሔ የሚሰጥ መሆኑን አመላክተዋል።

ይህንንም ታሳቢ ባደረገ መንገድ ተቋሙን የማደራጀትና መዋቅር የመዘርጋት ሥራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል።

በቀጣይም የሰው ኃይል የማሟላት እንዲሁም ተጨማሪ ዳኞች እንዲሾሙ ጥያቄ የማቅረብ ሥራዎች እንደሚሰሩ ገልፀዋል።

የፍርድ ቤቱ መቋቋም ለካፒታል ገበያው ሥርዓት ጉልህ አስተዋጽዖ እንዳለው ገልጸው፤ እነዚህን የቅድመ-ዝግጅት ሥራዎች በቅርቡ በማጠናቀቅ ወደ ሥራ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
ፍርድ ቤቱ በሥራ ሂደት የሚፈጠሩ ስህተቶች እንዲሁም በባለሥልጣኑ የሚወሰዱ እርምጃዎችን በሙሉ የማየት ሥልጣን እንዳለው ገልጸዋል።

ፍርድ ቤቱ የሚሰጠው ውሳኔ የመጨረሻ አለመሆኑንና ለመደበኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ የሚባልበት ሥርዓት በአዋጁ መመላከቱንም ተናግረዋል።

የካፒታል ገበያ ሥርዓቱ ተዓማኒና ተደራሽ እንዲሁም በኢትዮጵያ ልማትና ብልጽግና ውስጥ የራሱን ጉልህ አስተዋጽዖ እንዲያበረክት በትኩረት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

ለዚህም ባለድርሻ አካላት የድርሻቸውን እንዲወጡና እንዲያግዙ ጥሪ አቅርበዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም