አውሮፓ ኅብረት በኢትዮጵያ ለፍትሕ ተቋማት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
አውሮፓ ኅብረት በኢትዮጵያ ለፍትሕ ተቋማት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገለጸ
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 20/2016(ኢዜአ)፡-የአውሮፓ ኅብረት የኢትዮጵያ መንግሥት የተጠያቂነትና ግልጸኝነት መርህን የተከተሉ ጠንካራ የፍትህ ተቋማት ለመገንባት የሚያደርገውን ጥረት ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኑን አስታወቀ።
የአውሮፓ ኅብረት ለመስክ ሥራ የሚውሉ 18 ተሽከርካሪዎችን ድጋፍ አድርጓል፡፡
የፍትሕ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር) እና በኢትዮጵያ የአውሮፓ ኅብረት ምክትል አምባሳደር ዴቪድ ክሪቫኔክ የቁልፍ ርክክብ አካሂደዋል።
ድጋፉ የአውሮፓ ኅብረት በኢትዮጵያ የወንጀል ፍትሕ ሥርዓቱን ለማሻሻል እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ2022 እስከ 2025 የቀረጸው ፕሮጀክት አካል ነው ተብሏል።
የፍትሕ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር) በዚሁ ጊዜ፤ ሕብረቱ ላበረከተው የተሽከርካሪ ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።
የአውሮፓ ኅብረት ድጋፍ በፍትሕ ሚኒስቴር ፍላጎት ሙያዊና የቴክኒክ ጥናት የተመሠረተ ድጋፍ መሆኑን ገልፀዋል።
የሕብረቱ የቁሳቁስና የገንዘብ ድጋፍም የወንጀል ፍትሕ አስተዳደር ሥርዓቱን ለማዘመን በሚወሰዱ የማሻሻያ እርምጃዎች አዎንታዊ ውጤት ይኖራቸዋል ብለዋል።
ተሽከርካሪዎቹ በተለይም የመስክ ሥራዎች ለመሳለጥ ከፍተኛ እገዛ እንደሚኖራቸውም ጠቁመዋል።
በቅርቡ አዲስ የወንጀል ሥነ-ሥርዓት ሕግ ፀድቆ ወደ ተግባር ይገባል ያሉት ሚኒስትሩ፤ የሥነ-ሥርዓት ሕጉን ለማስተዋወቅ፣ ለማስረጽና በተሟላ መልኩ ተግባራዊ ለማድረግ የአውሮፓ ኅብረት የድጋፍ ፕሮግራም ትልቅ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።
በኢትዮጵያ የአውሮፓ ኅብረት ምክትል አምባሳደር ዴቪድ ክሪቫኔክ፤ የፍትሕ ተቋማት መጠናከር ለሕግ የበላይነት፣ ሰብዓዊ መብቶችና መሠረታዊ የነፃነት መብቶች መከበር ወሳኝ ሚና ይኖራቸዋል ብለዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት በተጠያቂነትና ግልጽነት መርህ ጠንካራ የፍትሕ ተቋማት ለመገንባትና ፍትሕ ለሁሉም እንዲረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የአውሮፓ ኅብረት ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኑን ገልፀዋል።
አሁን ላይም የአውሮፓ ኅብረት የኢትዮጵያ ወንጀል ፍትህ ሥርዓት ሪፎርም ለመደገፍ የ15 ሚሊየን ዩሮ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው ድጋፉም የፍትሕ አገልግሎቱን ውጤታማ ለማድረግ ያስችላል ነው ያሉት።
በርክክብ ሥነ-ሥርዓቱ በኢትዮጵያ የአውሮፓ ኅብረት ልዑክ፣ የድጋፍ ሥምምነት የፕሮጀክት አፈጻጸም ሠራተኞችና የፍትሕ ሚኒስቴር ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ተከናውኗል።