ቀጥታ፡

የወባ በሽታ ጫና ያለባቸው ወረዳዎችን በመለየት የመከላከልና ቁጥጥር ሥራ እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 20/2016(ኢዜአ)፡-  ከፍተኛ የወባ በሽታ ጫና ያለባቸውን 222 ወረዳዎችን በመለየት የበሽታ መከላከልና ቁጥጥር ሥራ ተጠናክሮ እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ገለፀ።

ኢንስቲትዩቱ "የምዕተ-ዓመት ጥረት ለተሻለ ሕብረተሰብ ጤና" በሚል የ100ኛ ዓመት አልማዝ እዮቤልዩ ክብረ-በዓል የማስጀመሪያ መርኃ-ግብር አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጥቷል።

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር መሳይ ኃይሉ (ዶ/ር) በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ ኢንስቲትዩቱ የኅብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቅኝት፣ መከላከልና ምላሽ ሥራዎች እየሰራ ነው።

በበሽታ አምጪ ተህዋስያን የሚከሰቱ ተላላፊ በሽታዎች ላይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር የቁጥጥር ሥራ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህንንም ተከትሎ ከዚህ ቀደም የሚከሰቱ በሽታዎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተሰራው ሥራ ተጨባጭ ውጤት ማስገኘቱን ጠቅሰዋል።

በተለይም አገራዊ ስትራቴጂ በማዘጋጀት ወባን ለመከላከልና ለመቆጣጠር አመርቂ ውጤት መመዝገቡን ነው ያስረዱት።

እንዲያም ሆኖ ባለፉት ሦስት ዓመታት በዓለም አቀፍ ደረጃ በተለይ ከሰሃራ በታች ባሉ አገራት የወባ በሽታ ሥርጭት እየጨመረ ነው ብለዋል።

በአስተላላፊ ትንኞች የሚተላለፉ በሽታዎች ሲከሰቱ የመከላከልና ቁጥጥር ሥራ እየተሰራ ነው ያሉት ዶክተር መሳይ፤ የወባ በሽታ ላይ አገራዊ ንቅናቄ በመፍጠር እስከታችኛው መዋቅር ድረስ አደረጃጀት በማጠናከር በርካታ ሥራዎች እየተሰሩ እንደሆነ ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ 76 በመቶ የበሽታውን ጫና የሚሸፍኑ 222 ወረዳዎች ተለይተው በየቀኑ መረጃ በመለዋወጥ የመከላከልና ቁጥጥር ሥራው እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።


ወባን በመከላከል ውጤታማ የሆኑ ሥልቶችና በምርምር የኅብረተሰብ ጤና ምላሽ ሥራዎችን በማጠናከር የመከላከልና ቁጥጥር ሥራው ተጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል።

ኢንስቲትዩቱ በኢትዮጵያ የመጀመሪያ ከሆነው ባለአንድ ዓይን መመልከቻ ማይክሮስኮፕ ጀምሮ የኅብረተሰቡን ጤናና ደኅንነት ለመጠበቅ የሚያግዝ ዓለም የደረሰበት ደረጃ ላይ የደረሱ መሳሪያዎችን ያካተተ ቤተ-ሙከራ ያለው መሆኑን አንስተዋል።

ባለፉት 100 ዓመታት የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር፣ የአገራዊ የላቦራቶሪ አቅም ለመገንባትና ጥራት ያለው የላቦራቶሪ አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል።

ይህም ብቻ ሳይሆን ኢንስቲትዩቱ ለጤና ባለሙያዎች ሥልጠና እየሰጠ መሆኑን ጠቅሰው፤ በአፍሪካ ደረጃ የኅብረተሰብ ጤና የልህቀት ማዕከል ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

የ100 ዓመታት ክብረ-በዓሉም ኢንስቲትዩቱ የጀመራቸውን ውጤታማ ሥራዎች የሚያጠናክርበትና ያለውን አህጉርና ዓለም ዓቀፍ ትስስር አጠናክሮ የሚቀጥልበት መሆኑን ጠቁመዋል።

ኢንስቲትዩቱ ከመጪው ሰኔ 24 እስከ 28 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ የአልማዝ እዮቤልዩ ክብረ-በዓሉን በተለያዩ መርኃ-ግብሮች እንደሚያከብር ተመላክቷል።

ከጋዜጣዊ መግለጫው በተጨማሪ የምዕተ-ዓመቱን አከባበር በምን መልኩ ማክበር እንደታቀደ የሚያሳይ ገለፃ የተሰጠ ሲሆን፤ የኢንስቲትዩቱ ኃላፊዎች፣ የአርማወር ሐንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱና የተለያዩ ባለድርሻ አካላትም ተገኝተዋል።

በተጨማሪም የኢንስቲትዩቱን የምዕተ-ዓመት ጉዞ የሚያስቃኝ https.//anniversary.ephi.gov.et የሚል ድረ-ገፅም በይፋ ተከፍቷል።

የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የኅብረተሰብ ጤና አደጋዎችና የጤና ሥጋቶች ሲከሰቱ ተለዋዋጭ ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎችን እንዲሁም የጤና ሥጋቶች፣ የበሽታ አምጪ ተህዋስያንና አስተላላፊ ነፍሳት ሁኔታ ላይ ያልተቋረጠ የበሽታዎች ክትትልና ቁጥጥር ያደርጋል።

 

 
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም