ቀጥታ፡

የአነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንተርፕራይዝ ኢንቨስትመንት የንቅናቄ መድረክ ዛሬ በሠመራ ተካሂዷል

ሠመራ ፤ ሰኔ 20/2016(ኢዜአ)፦ የአነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንዱስትሪዎች ያሉንን ሀብቶች ለመጠቀም ከማገዛቸው ባለፈ የስራ እድል ለመፍጠር ጉልህ ድርሻ እንዳላቸው የኢትዮጵያ ኢንተርኘራይዝ ልማት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዱልፈታህ የሱፍ ገለጹ።

በኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት አስተባባሪነት የአነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንተርፕራይዝ ኢንቨስትመንት የንቅናቄ መድረክ ዛሬ በሠመራ ተካሂዷል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ኢንተርኘራይዝ ልማት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዱልፈታህ የሱፍ እንዳሉት የአነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንዱስትሪዎች ያሉን ሀብቶች ላይ እሴት በመጨመር በጥቅም ላይ ለማዋል ያግዛሉ።

ኢንተርፕራይዞቹ በተለይም ምርቶችን ከገበያ ጋር በማስተሳሰር ከሚያበረክቱት ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ በተጓዳኝ  የስራ እድል ለመፍጠርም ጉልህ ድርሻ አላቸው ብለዋል።

ኢንተርፕራይዞቹ በአምራች ዘርፉ ላይ እሴት የሚጨምሩ ሊሆኑ እንደሚገባ ያነሱት አቶ አብዱልፈታህ፤ በዚህ ረገድ የአመራሩ ቁርጠኝነት ከታከለበት የሚቻል መሆኑን ነው የገለፁት።

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ የኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪ አቶ ዓሊ መሐመድ በበኩላቸው የአፋር ክልል በእንስሳት ሃብት፣ በግብርና ውጤቶችና በማዕድን ሐብቶች የታደለ ክልል ነው ብለዋል።


 

በክልሉ በአነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች የተሻለ ውጤት ለመመዝገብ የሚያስችሉ ተግባራት በመከናወን ላይ መሆናቸውን አቶ ዓሊ አንስተዋል። 

የአነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንተርፕራይዞች በውስን ካፒታልና ሰፊ የሰው ሃይል በማሳተፍ እነዚህን የተፈጥሮ ሀብቶችን እሴት በሚጨምር መልኩ ማቀናበርና ማምረት ዋነኛ ሥራቸው ሊሆን ይገባል ብለዋል።

በዚህም ዘላቂነት ያለው የስራ ዕድል ለመፍጠርና የወጪ ንግድን በማሳደግ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታቸው የጎላ ነው ብለዋል።


 

ክልሉም ያሉትን ጸጋዎችና የተፈጥሮ ሀብቶቹን በአግባቡ በመጠቀም ለክልሉ ብሎም ለአገር ኢኮኖሚ እንዲውሉ ለማድረግ የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

በቀጣይነትም የአምራች ኢንዱስትሪውን ዘርፍ  ለማነቃቃት ከተለያዩ አስፈፃሚ አካላትና ባለድርሻ አካላት ጋር የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አክለዋል።

ይህንን ለማገዝ ክልሉ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ እንደገና እንዲደራጅ ማድረጉን ገልፀው ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር በመተባበርም ፍኖተ ካርታ እየተዘጋጀ መሆኑን አቶ ዓሊ አስታውቀዋል።

የአፋር ክልል ንግድ ገበያ ልማትና ኢንዱስትሪ ቢሮ የኢንዱስትሪ ዘርፍ ምክትል ሃላፊ አቶ ኢብሪሂም ዓሊም ክልሉ ወጣቶችን በማደራጀት በተለያዩ ኢንርፕራይዞች ተሳታፊ ለማድረግ እየተሰራ ያለው ሥራ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ገልጸዋል።


 

በአፋር ክልል ደረጃ 21 መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች ያሉ ሲሆን፤  169 አነስተኛ ኢንዱስትሪዎች እንደሚገኙ ከክልሉ ንግድ፣ ገበያ ልማትና ኢንዱስትሪ ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

በዚህ መድረክ የፌዴራልና የአፋር ክልል ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ታድመዋል።

  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም