ቀጥታ፡

የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ማኅበረሰቡ ኃላፊነቱን  እንዲወጣ ጥሪ ቀረበ 

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 20/2016(ኢዜአ)፦ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ማኅበረሰቡ  ኃላፊነቱን  እንዲወጣ የትምህርት ሚኒስቴር ጠየቀ። 

የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር 11ኛውን የትምህርት ጥራት ኮንፍረንስ እንዲሁም "የሕዝብ ፈንድ ለትምህርት" ዘመቻን ዛሬ በይፋ አስጀምሯል።

የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ አየለች እሸቴ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ የሀገሪቱን ሁለንተናዊ እድገት ለማሳለጥ የትምህርት ጥራት ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥተን መሥራት ይገባል ብለዋል።

ሚኒስቴሩም በአሁኑ ሰዓት የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የመምህራንን አቅም የማጎልበትና "ትምህርት ለትውልድ" የትምህርት ቤቶችን ደረጃ የማሻሻል ሥራ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ ከ25 ቢሊዮን ብር በላይ  ማሰባሰብ መቻሉን ጠቅሰው በርካታ ትምህርት ቤቶችን ደረጃ የማሻሻል፣ አዳዲስ ትምህርት ቤቶችን የመገንባትና ግብዓቶችን የማሟላት ሥራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። 

የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የተወሰነ አካል በተወሰነ ጊዜ ብቻ የሚወጣው ተግባር ባለመሆኑ መምህራን ብሎም የትምህርት ማኅበረሰቡ የሚጠበቅባቸውን ሀገራዊ አደራ ከምንጊዜውም በላይ መወጣት አለባቸው ብለዋል።


 

የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር ፕሬዝዳንት ዮሐንስ በንቲ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ማኅበሩ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ መምህራን ግንባር ቀደም ተሳታፊ ሆነው ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል ነው ያሉት።

በዛሬው ዕለት ማኅበሩ በሚያደርገው 11ኛው የትምህርት ጥራት ኮንፍረንስ ላይ የትምህርት ጥራትን ማሻሻል በሚያስችሉ አጀንዳዎች ምክክር ይደረጋል ብለዋል።

በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ከዚህ ቀደም ላስጀመሩት ትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ ማኅበሩ ድጋፍ ማድረግ የሚያስችለውን "የሕዝብ ፈንድ ለትምህርት" በሚል መሪ ኃሳብ ዘመቻ ዛሬ ማስጀመሩን ጠቁመዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም