መንግሥት ለሕክምና ግብዓት አምራቾች እያደረገ ያለው ድጋፍ ዘርፉ እንዲነቃቃ አድርጓል - ኢዜአ አማርኛ
መንግሥት ለሕክምና ግብዓት አምራቾች እያደረገ ያለው ድጋፍ ዘርፉ እንዲነቃቃ አድርጓል

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 20/2016 (ኢዜአ)፦መንግሥት ለሀገር ውስጥ ሕክምና ግብዓት አምራቾች እያደረገ ያለው ድጋፍ ዘርፉን እንዲነቃቃ ማድረጉን ኢዜአ ያነጋገራቸው ከፍተኛ መድኃኒት አምራች ኩባንያዎች ገለጹ።
በቂሊንጦ ፋርማሲዩቲካል ኢንዱስትሪ ፓርክ የተቋቋመው የአፍሪኩዩር መድኃኒት ፋብሪካ ባለቤትና ዋና ሥራ አስኪያጅ ታደሰ ተፈሪ (ዶ/ር) የፋርማሲዩቲካል ዘርፉ ዕድል ተመቻችቶለታል ይላሉ።
መንግሥት በፋይናንስ፣ በውጭ ምንዛሬ አቅርቦት፣ ከቀረጥ ነፃ የግብዓት ማስገባትና መሰል ማበረታቻዎችም ዘርፉ በከፍተኛ ደረጃ ዕድገት እንዲያሳይና እንዲነቃቃ ማስቻሉን ተናግረዋል።
በሀገር ውስጥም ሆነ በጎረቤት ሀገራት ከፍተኛ ገበያ እንዳለ የሚያነሱት ዶክተር ታደሰ፤ ለሀገር ውስጥ አምራቾች የተሰጠው ዕድል የገበያ ፍላጎቱን በቅጡ ለመሸፈን እንደሚያስችል ነው የተናገሩት።
ፋብሪካው የሚያመርታቸው 43 መድኃኒቶች ብዙኃኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚጠቀማቸውና ሰፊ የገበያ ዕድል ያላቸው መሆኑን ጠቅሰው፤ መንግሥት ለዘርፉ የሰጠው ትኩረት ለፋብሪካዎች ትልቅ ዕድል መሆኑን ያነሳሉ።
ከተመሠረተ ከግማሽ ምዕተ-ዓመት በላይ ያስቆጠረው የኢትዮጵያ መድኃኒት ፋብሪካ የምርምርና ሥርፀት ኃላፊ ሰይፈ ሽመልስ፤ ፋብሪካቸው 120 ተኪ ምርቶችን በማምረት ትልቅ ሚና ይጫወታል ይላሉ።
ፋብሪካው አሥር ዓይነት አዳዲስ መድኃኒቶች እያመረተ መሆኑን ገልጸው፤ መንግሥት ለዘርፉ የሰጠው ትኩረት ለመድኃኒት ፋብሪካዎች ምርታማነት ትልቅ ዕድል ይፈጥራል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ከመድኃኒት ጥገኝነት እንድትላቀቅ መንግሥት ድጋፉን መቀጠል እንዳለበት ገልጸው፤ ባለኃብቶችም ዕድሉን ተጠቅመው በሕክምና ግብዓቶች ማምረት ላይ ሊሰማሩ እንደሚገባ አንስተዋል።
በ1997 ዓ.ም ምርት የጀመረው አዲስ መድኃኒት ፋብሪካ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ ዮሐንስ ፍስሐ በበኩላቸው፤ ፋብሪካው 100 የመድኃኒት ዓይነቶች እያመረተ በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረበ ነው ብለዋል።
ከውጭ ሀገር የሚገባውን ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዘው የሕክምና ግብዓት በሀገር ውስጥ ለመተካት መድኃኒትና የመድኃኒት ግብዓቶችን የሚያመርቱ ፋብሪካዎች እንዲስፋፉ ዕድል ይሰጣል ነው ያሉት።
ዘርፉ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት ቢጠይቅም መልሶ የሚከፍል በመሆኑ ባለኃብቶች በዘርፉ መዋዕለ-ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ጠይቀዋል።
በዘርፉ ጥራትና ብቃት ያለው የሰው ኃይል ማፍራት እንደሚገባም እንዲሁ።