የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ29ኛ ሣምንት መርኃ ግብር ዛሬ ይጀመራል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ29ኛ ሣምንት መርኃ ግብር ዛሬ ይጀመራል
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 20/2016(ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ29ኛ ሣምንት የመጀመሪያ ቀን ውሎ ሁለት ጨዋታዎች ይካሄዳሉ።
ሃዋሳ ከተማ ከባህር ዳር ከተማ ከቀኑ 9 ሰዓት በሃዋሳ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም ይጫወታሉ።
በአሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ የሚመራው ሃዋሳ ከተማ በፕሪሚየር ሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት 5 ተከታታይ ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው 1 ጊዜ ብቻ ነው። 2 ጊዜ ሲሸነፍ በተመሳሳይ 2 ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይቷል።
በእነዚህ 5 ጨዋታዎች 7 ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ 12 ጎሎችን አስተናግዷል።
ሃዋሳ ከተማ በ37 ነጥብ 11ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ባህር ዳር ከተማ ካለፉት 5 ጨዋታዎች 2 ጊዜ ሲያሸንፍ 3 ጊዜ ደግሞ ነጥብ ተጋርቷል። በ5ቱ ጨዋታዎች 7 ግቦችን ሲያስቆጥር 4 ጎሎች ተቆጥረውበታል።
በደግአረገ ይግዛው የሚሰለጥነው ባህር ዳር ከተማ በ49 ነጥብ 4ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ሁለቱ ክለቦች በሊጉ በመጀመሪያው ዙር ባደረጉት ጨዋታ ባህር ዳር ከተማ 2 ለ 1 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።
በሌላኛው የ29ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ድሬዳዋ ከተማ ከሲዳማ ቡና ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ድሬዳዋ ከተማ ካለፉት 5 የሊግ ጨዋታዎች 2 ጊዜ ድል ሲቀናው በተመሳሳይ 2 ጊዜ ተሸንፏል። 1 ጊዜ አቻ ወጥቷል።
ድሬዳዋ በ5ቱ ጨዋታዎች 6 ግቦችን ሲያስቆጥር 9 ጎሎችን አስተናግዷል።
በኮማንደር ሽመልስ አበበ የሚመራው ድሬዳዋ ከተማ በ40 ነጥብ 8ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
ተጋጣሚው ሲዳማ ቡና በሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች ያሸነፈው 1 ጊዜ ብቻ ነው። 3 ጊዜ ሲሸነፍ 1 ጊዜ አቻ ወጥቷል።
በነዚህ 5 ጨዋታዎች 5 ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ 8 ግቦችን አስተናግዷል።
በዘላለም ሽፈራው የሚሰለጥነው ሲዳማ ቡና በ34 ነጥብ 12ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያው ዙር ባደረጉት የሊጉ ጨዋታ ድሬዳዋ ከተማ 2 ለ 0 ማሸነፉ አይዘነጋም።
የ29ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ነገም ቀጥሎ ሲውል ኢትዮጵያ መድን ከሀድያ ሆሳዕና ከቀኑ 9 ሰዓት ፣ ከፕሪሚየር ሊጉ መውረዱ የተረጋገጠው ሀምበሪቾ ከወልቂጤ ከተማ ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያከናውናሉ።
የ29ኛ ሳምንት ጨዋታዎች እስከ ሰኔ 23 ቀን 2016 ዓ.ም ይቆያሉ።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሪሚየር ሊጉን በ58 ነጥብ ይመራል። መቻል በ57 ነጥብ ይከተላል።
የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን ኤርትራዊው የሃዋሳ ከተማ አጥቂ አሊ ሱሌማን በ17 ግቦች እየመራ ነው።
የመቻል አጥቂ ምንይሉ ወንድሙ በ14 እና የአዳማ ከተማው የፊት መስመር ተሰላፊ ዮሴፍ በ12 ግቦች ይከተላሉ።