ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ እና የኮሪያ ሪፐብሊክ ወታደራዊ ግንኙነት ተጠናክሮ ይቀጥላል - ኢንጂነር አይሻ መሀመድ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 20/2016(ኢዜአ)፦ ለዘመናት ዓለምን ያስደነቀው የኢትዮጵያ እና የኮሪያ ሪፐብሊክ ወታደራዊ ግንኙነት ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ የመከላከያ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሀመድ ገለጹ፡፡

የመከላከያ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሀመድ በኢትዮጵያ፣ በጂቡቲ እና በሲሸልስ የኮሪያ ሪፐብሊክ አምባሳደር እና የአፍሪካ ህብረት ቋሚ ተወካይ ካንግ ጁንግ ጋር በቢሯቸው ተወያይተዋል፡፡

በውይይቱም የኢትዮጵያ እና የኮሪያ ሪፐብሊክ የቀደመ ታሪካዊ እና ወታደራዊ ግንኙነት ምን ይመስል እንደነበር ምክክር ተደርጎበታል፡፡

እነዚህ የረጅም ጊዜ ብቻ ሳይሆን ዘመን የማይሽረው ታሪካዊ ግንኙነት የነበራቸው ሁለት ሀገራት የቀደመውን ግንኙነት በማደስ በወታደራዊ እና ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ የበለጠ በትብብር እና በጥምረት ሊሰሩ እንደሚገባ በስፋት ተነስቷል፡፡

የኢትዮጵያ መከላከያ ሚኒስቴር ከ116 ዓመታት በላይ ረጅም ዕድሜ ያለው እና በእነዚህ ረጅም ዓመታትም በርካታ ሀገራዊ መሰረቶችን እየሰራ የመጣ አንጋፋ ተቋም በመሆኑ የሀገሪቱ ታላቅ ቅርስ መሆኑን ሚኒስትሯ ኢንጂነር አይሻ መሀመድ ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም መከላከያ ይህን አንጋፋነቱን ማረጋገጥ የሚችሉ ወታደራዊ ቅርሶች እና መረጃዎች በዘመናዊ መልኩ ሰንዶ ማስቀመጥ የሚያስችል ወታደራዊ ሙዚየም ለመገንባት ጠንክሮ እየሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡

ይህን ታላቅ ሀገራዊ ስራ ደግሞ የረጅም ጊዜ ግንኙነት ካለን ከኮሪያ ሪፐብሊክ እና ከመሰል ወዳጆቻችን ጋር በጋራ ለመስራት እንቅስቃሴ እያደረግን ነው ሲሉም አክለዋል፡፡

አምባሳደር ካንግ ጁንግ በበኩላቸው የኮሪያ ሪፐብሊክ ወታደራዊ ታሪክ ከኢትዮጵያ ወታደሮች ጋር የተቆራኘ ነው ብለዋል፡፡


 

ሀገራችን አሁን ለደረሰችበት ቁመና የኢትዮጵያ ወታደሮች የከፈሉት ዋጋ ሁሌም ታሪክ ሲዘክረው የሚኖር ክቡር ተግባር ነው ሲሉም አክለዋል፡፡

በመሆኑም ከኢትዮጵያ ጋር መስራት፣ ተሞክሮ መለዋወጥ እና ወታደራዊ ትብብር ማድረግ እጅግ የሚያስደስት እና የምንኮራበት ተግባር ነው ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ በኩል ለሚደረጉ ማናቸውም ወታደራዊ እና ሀገራዊ እንቅስቃሴ እኛም በሙሉ ልብና ፈቃደኝነት እንሰራለን ሲሉ አምባሳደሩ መናገራቸውን ከመከላከያ ሰራዊት ማህበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም