ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በወታደራዊ አመራር መስክ የምታከናውናቸው ተግባራት ለአፍሪካውያን በምሳሌነት የሚጠቀሱ ናቸው - ሜጀር ጄኔራል ኢብራሂም ሚካኤል

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 20/2016(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በወታደራዊ አመራር መስክ በስትራቴጂክ ዕቅድ የምታከናውናቸው ተግባራት ለአፍሪካውያን በምሳሌነት የሚጠቀሱ መሆናቸውን የታንዛኒያ የዘመቻና የስልጠና ሀላፊ ሜጀር ጀኔራል ኢብራሂም ሚካኤል ገለጹ።

በታንዛኒያ የዘመቻና የስልጠና ሀላፊ ሜጀር ጀኔራል ኢብራሂም ሚካኤል እና በአየር ሀይሉ አዛዥ በሜጀር ጄኔራል ሻባኒ ባራንጋሽ የተመራ ከፍተኛ ወታደራዊ ልዑክ የመከላከያ አዛዥነትና ስታፍ ኮሌጅ የስራ እንቅስቃሴን ጎብኝቷል።

በጉብኝቱም የኮሌጁን የመማር ማስተማር ዘዴና በሚቀጥሉት ዓመታት ኮሌጁ ሊተገብር ባቀዳቸው ጉዳዮች ዙሪያ በኮሌጁ አዛዥ ብርጋዲየር ጄኔራል ሙሉጌታ አምባቸውና በከፍተኛ አመራሮች ገለፃ ተደርጎላቸዋል ።


 

ኮሌጁ በአጭርና በመደበኛ ኮርሶች ከኢትዮጵያ እና ከብዙ የአፍሪካ ሀገራት ለተውጣጡ ወታደራዊ አመራሮች ስልጠና እየሰጠ እንደሚገኝ የኮሌጁ አዛዥ ጠቁመዋል።

ኮሌጁን በአፍሪካ ካሉ ፕሮፌሽናል ወታደራዊ አመራር ማፍሪያ ማዕከላት መካከል ተወዳዳሪና ተመራጭ እንዲሆን ለማድረግ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙም ገልጸዋል።

የአዛዥነት እና ስታፍ ኮሌጅ አዛዥ ብርጋዲየር ጄኔራል ሙሉጌታ አምባቸው በቀጣይ በትምህርትና ወታደራዊ ስልጠና መስኩ ከታንዛኒያ ጋር በትብብር በመስራትና ልምድ በመለዋወጥ ያላቸውን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ፍላጎት እንዳላቸው አስታውቀዋል።


 

የታንዛኒያ ወታደራዊ ልዑክ መሪ ሜጀር ጄኔራል ኢብራሂም ሚካኤል ኮሌጁ ተለዋዋጭ የሆነውን አለም አቀፍና አካባቢያዊ ስጋቶችንና ቴክኖሎጂያዊ ለውጦችን በሳይንሳዊ ዘዴ በመተንተን እየሰጠ ላለው ስልጠና ያላቸውን አድናቆት ገልፀዋል።

በኮሌጁ ባዩት ነገር ደስተኛ መሆናቸውን የገለፁት የልዑኩ መሪ ኮሌጁ የስትራቴጂክ ዕቅድ በመያዝ እያከናወናቸው ያሉት ተግባራት ለአፍሪካውያን በምሳሌነት የሚጠቀስ መሆኑን ጠቁመዋል።

በቀጣይም ከኮሌጁ ጋር በትብብር መስራታቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የገለፁት ጄኔራል መኮንኑ በኮሌጁ እየተማሩ የሚገኙ የታንዛኒያ ተማሪዎችንም አበረታተዋል።

በመጋቢት ወር በታንዛኒያ መከላከያ አዛዥነትና ስታፍ ኮሌጅ አዛዥ የተመራ ልዑክ በኢትዮጵያ የመከላከያ አዛዥነትና ስታፍ ኮሌጅ ጉብኝት ማድረጉን ከኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ማህበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም