ኢትዮጵያ እና ደቡብ ሱዳንን የሚያገናኝ የ220 ኪሎ ሜትር መንገድ ሊገነባ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ እና ደቡብ ሱዳንን የሚያገናኝ የ220 ኪሎ ሜትር መንገድ ሊገነባ ነው

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 20/2016(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ እና ደቡብ ሱዳን እ.ኤ.አ በግንቦት 2023 የተፈራረሙትን የ738 ሚሊዮን ዶላር የፋይናንስ ስምምነት ተከትሎ ሁለቱን ሀገራት የሚያገናኝ 220 ኪሎ ሜትር መንገድ ሊገነቡ ነው።
የደቡብ ሱዳን ብሔራዊ የሽግግር ህግ አውጪ ምክር ቤት የኢትዮጵያ-ደቡብ ሱዳን ድንበር ተሻጋሪ መንገድ ለመገንባት የተፈረመውን የገንዘብ ስምምነት አጽድቋል።
ፕሮጀክቱ በኢትዮጵያ እና በደቡብ ሱዳን መካከል እያደገ ያለውን ትብብር እና የጋራ ተጠቃሚነት ግንኙነት በማሳየት የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ እና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነትን ለማጠናከር ያለመ ነው።
ስምምነቱ በጉባዔው በሙሉ ድምጽ ተቀባይነት ካገኘ በኋላ ለፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር የመጨረሻ ፍቃድ መቅረቡን የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።