የዘንድሮው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ኮከብ ተጫዋች እጩዎች ይፋ ሆኑ - ኢዜአ አማርኛ
የዘንድሮው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ኮከብ ተጫዋች እጩዎች ይፋ ሆኑ
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 19/2016(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማህበር የ2016 የሊጉን ኮከብ ተጫዋች እጩዎች ዝርዝር ዛሬ ይፋ አድርጓል።
ተመልካቾች ለተጫዋቾች ድምጽ መስጠት የሚችሉበት አማራጭ ማዘጋጀቱንም ገልጿል።
የሊጉ አክሲዮን ማህበር ለኮከብ ተጫዋችነት ሽልማት 7 እጩ ተጫዋቾችን አሳውቋል።
የመቻል የአማካይ ተጫዋቾች ሽመልስ በቀለና ከነዓን ማርክነህ ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አምበል ፈቱዲን ጀማልና ጋናዊው የክለቡ አማካይ ተጨዋች ባሲሩ ዑመር ፣ የባህር ዳር ከተማው የክንፍ መስመር ተጫዋች ቸርነት ጉግሳ፣ የወላይታ ድቻ አጥቂ ቢንያም ፍቅሬና ኤርትራዊው የሃዋሳ ከተማ የፊት መስመር ተሰላፊ አሊ ሱሌማን በእጩነት ቀርበዋል።
በኮከብ ወጣት ተስፈኛ ተጨዋች ዘርፍ ወገኔ ገዛኸኝ ከኢትዮጵያ መድን፣ ተመስገን ብርሃኑ ከሀድያ ሆሳዕና፣ ዮሐንስ መንግስቱ ከመቻል፣ በፍቃዱ አለማየሁ ከኢትዮጵያ ቡናና መድን ተክሉ ከወልቂጤ ከተማ እጩዎች ዝርዝር ውስጥ ገብተዋል።
ፍሬው ጌታሁን ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ አቡበከር ኑራ ከኢትዮጵያ መድንና ሰዒድ ሀብታሙ ከአዳማ ከተማ የኮከብ ግብ ጠባቂ እጩዎች ናቸው።
ተመልካቾች በተለያየ ዘርፍ የቀረቡትን ተጫዋቾች እስከ ሰኔ 28 ቀን 2016 ዓ.ም መምረጥ እንደሚችሉና በ https://t.me/ethiopianlea/17849 የአክሲዮን ማህበሩ የቴሌግራም ገጽ ድምጽ መስጠት እንደሚችሉ ጠቁሟል።