ቀጥታ፡

በጤናው ዘርፍ የተሰማሩ አነስተኛና መካከለኛ አምራቾችን በመደገፍ የሀገር ውስጥ ምርትን ለማበረታታት የተጀመሩ ስራዎች ይበልጥ ሊጠናከሩ ይገባል

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 19/2016(ኢዜአ)፦ በጤናው ዘርፍ የተሰማሩ አነስተኛና መካከለኛ አምራቾችን በመደገፍ የሀገር ውስጥ ምርትን ለማበረታታት የተጀመሩ ስራዎች ይበልጥ ሊጠናከሩ እንደሚገባ ተገለጸ፡፡

የሀገር ውስጥ የሕክምና ግብዓት ምርትና ኢኖቬሽን ዐውደ ርዕይ ከአምስት ቀናት በፊት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተመርቆ ለእይታ ክፍት መሆኑ ይታወቃል፡፡

በአውደ ርዕዩም የሕክምና ግብዓት አምራቾች፣የምርምር ተቋማት፣ የጥራት ተቆጣጣሪና የሎጀስቲክስ አገልግሎት ሰጭ ተቋማት እየተሳተፉ ሲሆን  በርካታ ዜጎችም እየጎበኙት ይገኛል፡፡

ከአውደ ርዕዩም ጎን ለጎን በተለያዩ ርዕሶች የፓናል ውይይቶች እየተካሄደ ሲሆን በዛሬው ዕለት በዘርፉ ያሉ አነስተኛ እና መካከለኛ አምራች ኢንዱስትሪዎችን መደገፍ እና ግብዓት ማቅረብ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር የፓናል ውይይት ተካሂዷል።

በፓናል ውይይቱ የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን፣ የኢትዮጵያ ኬሚካል ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን፣ የአርማወር ሃንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ኮርፖሬሽን  እና የኢትዮጵያ ቆዳ እንክብካቤ እና መድኃኒት አምራቾች ማህበር አመራሮችና ተወካዮች ተሳትፈዋል፡፡

የአገር ውስጥ የህክምና ግብዓት ምርትን ለማሳደግ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት አበረታች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ስዩም ወልዴ በዚሁ ውቅት አነስተኛ እና መካከለኛ የመድኃኒት አምራቾች ጥራት ያለው ምርት እንዲያመርቱ እና ውጤታማነታቸውን ለማረጋገጥ አስፈላጊ የሆኑ ቁጥጥር እና ክትትል እንደሚደረግላቸው አስረድተዋል።

ይህም ጥራት ያለው ምርት ለገበያ እንዲቀርብ በማድረግ ዘርፉ እንዲነቃቃ ምቹ እድል እንደሚፈጥር ተናግረዋል፡፡


 

የአርማወር ሃንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት ምክትል ዳይሬክተር መሳይ ወልደማርያም በበኩላቸው ኢንስቲትዩቱ በዘርፉ ያሉ አምራች ኢንዱስትሪዎችን በጥናትና ምርምር ስራው እየደገፈ መሆኑን ገልፀዋል።

በቀጣይ አምራች ኢንዱስትሪዎች ምርታነት ለማሳደግ የጥናትና ምርምር ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።


 

የኢትዮጵያ ኬሚካል ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን ለፋርማሲዩቲካል አምራች  ኢንዱስትሪዎች ግብዓት የሚሆኑ የተለያዩ ኬሚካሎችን በማምረት እያቀረበ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የኮርፖሬሽን ስራ አስፈፃሚ ዶክተር ሁንዴሳ ደሳለኝ (ዶ/ር) ናቸው፡፡

በዚህም ኮርፖሬሽኑ ሃይድሮጂን ፐርኦክስይድ፣ አሉሙኒየም ሳልፌት፣ ሰልፈሪክ አሲዲ እና የህክምና ጓንት ማምረቻ የሚሆን የጎማ ዛፍ እያመረተ መሆኑን ጠቅሰው፤ በዘርፉ ያለውን የግብዓት እጥረት ለመቅረፍ ሚናው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አሁን  ላይም በዘርፉ ያለው የሀገር ውስጥ ምርት እየተነቃቃ መሆኑን ተናግረዋል፡፡


 

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን  ምክትል ዳይሬክተር ከማል ኢብራሂም፤ በፋርማሲዩቲካል ኢንዱስትሪ ያለውን የማምረቻ ቦታ ችግር ለመቅረፍ ለአምራች ኩባንያዎች አስፈላጊ የሆኑ መሰረተ ልማቶችን እያቀረበ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ለአብነትም ኮርፖሬሽኑ በቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ 279 ሄክታር መሬት ለፋርማሲዩቲካል አምራቾች ማዘጋጀቱን ተናግረዋል።

በሀገር ውስጥ ያሉ የዘርፉ አምራች ኩባንያዎች በኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ በመግባት ኢንቨስት እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።


 

የኢትዮጵያ የቆዳ እንክብካቤ እና መድኃኒት አምራቾች  ማህበር ፕሬዝዳንት ሀሺም አህመድ በበኩላቸው የመስሪያ ቦታ፣ የካፒታል እና  የመሰረተ ልማት እጥረት የዘርፉ እድገት ማነቆ ሆኖ መቆየቱን ጠቅሰዋል፡፡

መንግስት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለዘርፉ በሰጠው ትኩረት ችግሮቹ ደረጃ በደረጃ እየተቀረፉ መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡

ለአብነትም የቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ የማምረቻ ቦታ እጥረትን በመቅረፍ ረገድ ትልቅ እድል ይዞ መምጣቱን ጠቅሰዋል፡፡

የጤናው ዘርፍ ግብዓት አምራቾችን በአንድ እንደ ኢንዱስትሪ ፓርክ ባሉ የማምረት ማእከላት ማሰባሰብ በቀላሉ ድጋፍ እንዲያገኙ አንደሚያደርግም ነው የጠቀሱት፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም