ተቋማት ወጪ ቆጣቢ የበጀት አጠቃቀም ሥልቶችን ተግባራዊ በማድረግ የሚመደብ በጀትን በአግባቡ ሥራ ላይ ማዋል አለባቸው - ቋሚ ኮሚቴው    

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 19/2016(ኢዜአ)፦ ተቋማት ወጪ ቆጣቢ የበጀት አጠቃቀም ሥልቶችን ተግባራዊ በማድረግ የሚመደብ በጀትን በአግባቡ ሥራ ላይ ማዋል እንደሚገባቸው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።  

ቋሚ ኮሚቴው ለ2017 በጀት ዓመት በቀረበው ረቂቅ በጀት ዙሪያ ይፋዊ የሕዝብ ውይይት ያካሄደ ሲሆን፤ በመድረኩም የፌደራል ተቋማት እና የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡

በውይይቱ ላይ ረቂቅ በጀቱ ታሳቢ ያደረጋቸው ጉዳዮች፣ በጀት አመዳደብ እና መነሻ ጉዳዮች ላይ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ እዮብ ተካልኝ(ዶ/ር) ማብራሪያ ሰጥተዋል።     


 

በማብራሪያቸውም 2017 በጀት ዓመት ረቂቅ በጀት 971 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ሆኖ መቅረቡን ጠቅሰው፤ በጀቱ የኢኮኖሚ ዕድገቱን፣ የዋጋ ግሽበትን፣ ወጪና ገቢ በዝርዝር በመገምገም መዘጋጀቱንም አስረድተዋል።

በዚሁ መሰረት ጠቅላላ ገቢ እና እርዳታ እቅድ 612 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር መሆኑን ጠቁመው ከዚሁ ውስጥ አብዛኛው በታክስ ገቢ የሚሸፈን መሆኑንም አመልክተዋል።   

የታክስ ገቢው 502 ቢሊዮን ብር እንዲሆን መታቀዱን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው ይህም ከ2016 በጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ23 በመቶ ብልጫ አለው ብለዋል።    

ለበጀቱ የሚያስፈልገውን ገቢ በተሻለ መልኩ ለመሰብሰብ መንግሥት በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን ገልጸው ለዚህም የታክስ ማሻሻያ ሥራዎችን በአብነት ጠቅሰዋል።   

በውይይቱ የተሳተፉ የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ለሚ ጉታ(ዶ/ር) በሰጡት አስተያየት ዩኒቨርሲቲዎች ለተማሪዎች ከሚያቀርቡት የምግብ ቀለብ ጋር በተያያዘ እጥረት እየገጠመ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ 


 

ከዚህ አኳያ በጀቱ መሰል ጉዳዮችን ከግምት ያስገባ ሊሆን ይገባል ብለዋል።   

የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ብርሃነ መስቀል ጠና(ዶ/ር) በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ከኮሌጅ ወደ ዩኒቨርሲቲ እንዲያድግ ከተወሰነ ወዲህ ግንባታዎችን ጨምሮ የማሻሻያ እርምጃዎች እየተወሰዱ መሆኑን ጠቅሰዋል።


 

ይሁን እንጂ የፋይናንስ እጥረት ሥራዎች ላይ አሉታዊ ጫና እንዳይፈጥር የበጀት አመዳደቡ ላይ ከግምት ሊገባ ይገባል ሲሉ አመልክተዋል።

የፌደራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ተወካይ ደጀኔ ደቦጭ ከዚህ ቀደም በጀት አጠቃቀም ላይ ችግር የተስተዋለባቸው መስሪያ ቤቶች በአሁኑ በጀት እንዴት ይስተናገዳሉ? ሲሉ ጠይቀዋል።   

ከታክስ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ ከታክስ ስወራዎችና ማጭበርበር ጋር የተያያዙ ችግሮችን መከላከል ላይ ትኩረት መሰጠት እንዳለበትም እንዲሁ፡፡      

በገንዘብ ሚኒስቴር የበጀት ጉዳዮች አማካሪ አቶ ተፈሪ ደመቀ በሰጡት ማብራሪያ ከዩኒቨርሲቲዎች የቀለብ አቅርቦት ጋር በተያያዘ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት ጥናት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።


 

ጥናቱ ትምህርት ከመጀመሩ በፊት እንደሚጠናቀቅና ጥናቱን መሰረት በማድረግ የሚደረገው ማሻሻያ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ጸድቆ ሥራ ላይ እንዲውል እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።  

የዩንቨርሲቲ ግንባታ ፕሮጀክቶችን በተመለከተም ጠቀሜታቸው ከፍ ያሉትን በለመየት በጀት የመመደብ ሥራዎች እንደሚናወኑ ገልጸዋል።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ደሳለኝ ወዳጄ፤ ተቋማት ወጪ ቆጣቢ የበጀት አጠቃቀም ሥልቶችን ተግባራዊ በማድረግ የሚመደብ በጀትን በአግባቡ ሥራ ላይ ማዋል እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል፡፡


 

በዚህም የኃብት ብክነትን የሚያስቀር አሰራር ሊከተሉ እንደሚገባ በማሳሰብ።

የመስኖ የመንገድና ሌሎች ካፒታል ፕሮጀክቶች ላይም የሚስተዋሉ መጓተቶችን የሚያስቀሩ ሥልቶችን ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባም ነው ያመለከቱት።

ለዚህም ታክስ አሰባሰብ ላይ የሚከናወኑ ተግባራት ሊጠናከሩ ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም