የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር እና የኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ በትብብር ለመስራት ተስማሙ - ኢዜአ አማርኛ
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር እና የኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ በትብብር ለመስራት ተስማሙ
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 19/2016(ኢዜአ)፦ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር(ኢመደአ) እና የኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ በጋራ በሚሰሩባቸው ጉዳዮች ላይ የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ።
በስምምነቱ ወቅት የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ዳንኤል ጉታ እንደገለጹት ተቋማቸው የኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ የሀገራችንን የስኳር ፍላጎት ከማሟላት ባሻገር ለውጭ ገበያ ለማቅረብ በሚያደርጋቸው ጥረቶች ሁሉ አስፈላጊውን እገዛ ያደርጋል።
በዚህም የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር በራሱ አቅም ባለማቸው ቴክኖሎጂዎች እና የሰው ሀይሉን በማሰልጠን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዋዮ ሮባ በበኩላቸው አሁን ላይ በሀገር አቀፍ ደረጃ ያለውን የስኳር ፍላጎት ለመሽፈን በተለምዷዊው አካሄድ መሄድ አዋጭ አለመሆኑን በመረዳት ተቋማቸው ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን ወደ መጠቀም መምጣቱን ገልጸዋል።
ለዚህም እንደ ኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር በመሳሰሉ በዘርፉ የካበተ ልምድ ካላቸዉ ተቋማት ጋር በትብብር መስራት ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።
የኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች ከመግባቢያ ስምምነቱ ባሻገር የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ምርትና አገልግሎቶችን እንዲሁም የኢትዮ ሳይበር ታለንት ማዕከልን መጎብኘታቸውን ከኢመአድ ማህበራዊ ትስስር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።