ቀጥታ፡

በቂሊንጦ ፋርማሲዩቲካል ኢንዱስትሪ ፓርክ ከገቡ የሕክምና ግብዓት አምራች ኩባንያዎች መካከል አምስቱ ምርታቸውን ለገበያ እያቀረቡ ነው

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 19/2016(ኢዜአ)፦ በቂሊንጦ ፋርማሲዩቲካል ኢንዱስትሪ ፓርክ ከገቡ የሕክምና ግብዓት አምራች ኩባንያዎች መካከል አምስቱ ምርታቸውን ለገበያ ማቅረብ መጀመራቸውን የፓርኩ አስተዳደር አስታወቀ።

የኢትዮጵያ የፋርማሲዩቲካል አምራቾች ማህበር በበኩሉ መንግስት ለፋርማሲዩቲካል ዘርፍ የሰጠው ትኩረት ኢትዮጵያ በሕክምና ግብዓት ራሷን እንድትችል ትልቅ ተስፋ የሚሰጥ መሆኑን ገልጿል።

በኢንዱስትሪ ፓርኮች ኮርፖሬሽን የቂሊንጦ ፋርማሲዩቲካል ኢንዱስትሪ ፓርክ ምክትል ስራ አስኪያጅ አሊያ ሃዋስ ለኢዜአ እንደተናገሩት ኢንዱስትሪ ፓርኩ ከኢትዮጵያ አልፎ ለምስራቅ አፍሪካ የፋርማሲዩቲካል ማዕከል እንደሆነ ተናግረዋል።

ፓርኩ ወደ ስራ ከገባ እስካሁን በመድሀኒት እና መድሀኒት ነክ ምርቶችን ለማምረት ፈቃድ የወሰዱ 21 ኩባንያዎች ወደ ፓርኩ ገብተው እያለሙ መሆኑን ተናግረዋል።

ከእነዚህም መካከል የመድሃኒት እና መድሃኒት ነክ የሕክምና ግብቶችን የሚያመርቱ አምስት ኩባንያዎች የማመረት ሂደታቸውን ጨርሰው ምርታቸውን ለገበያ ማቅረብ ጀምረዋል ነው ያሉት።

የቂሊንጦ ፋርማሲዩቲካል ኢንዱስትሪ ፓርክ በዘርፉ የሚያጋጥሙ የቢሮክራሲ እና የመሰረተ ልማት ተግዳሮቶችን በማቃለል አምራቾች ውጤታማ እንዲሆኑ ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ 80 በመቶ የሕክምና ግብዓቶችን ከውጭ ስታስገባ መቆየቷን ገልፀው፤ መንግስት ይህን ክፍተት ለመቅረፍ በሀገር ውስጥ እንዲመረቱ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው ብለዋል።

በቀጣይም በፋርማሲዩቲካል ዘርፍ ለሚሰማሩ ኩባንያዎች ማበረታቻዎችን በማድረግ ከተኪ ምርቶች ባሻገር ወደ ሌሎች ሀገራት የሚላኩ የሕክምና ግብዓቶችን ማምረት እንደሚቻል ነው ያነሱት።


 

የኢትዮጵያ ፋርማሲዩቲካል አምራቾች ማህበር ፕሬዚዳንት ዶክተር ዳንኤል ዋቅቶላ በበኩላቸው መንግስት ለዘርፉ የሰጠው ትኩረት ኢትዮጵያ በሕክምና ግብዓት ራሷን እንድትችል የሚያደርግ ነው ብለዋል።

የሕክምና ግብዓቶች እንደ ሀገር ቀዳሚ ትኩረት እንደሚሹ ጠቅሰው፤ በዚህም መንግስት እና ባለድርሻ ተቋማትም በልዩ ትኩረት ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን ገልፀዋል።

ነገር ግን በጉምሩክ እና ሎጀስቲክስ ረገድ አሁንም መሻሻል ያሉባቸው ስራዎች መኖራቸውን ጠቅሰዋል፡፡

ለመድሃኒት ግብዓት የሚሆኑ ጥሬ ዕቃዎች በሀገር ውስጥ መኖራቸውን ጠቀሰው፤ ከሕክምና ግብዓቶች ባሻገር የመድሃኒት ግብዓቶችን የሚተኩ ምርቶችንም በሀገር ውስጥ በማምረት የውጭ ምንዛሬ ማዳን እንደሚቻል ጠቁመዋል።

በዚህም ኩባንያዎች ዘርፉን እንዲቀላቀሉ ዘላቂነት ያለው የፖሊሲ ድጋፍ እንደሚሻ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም