ቀጥታ፡

የኦሎምፒክ ችቦው በተተኪ ስፖርተኞች ዘንድ መነሳሳትን ለመፍጠር ሚናው የጎላ ነው-የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ 

ሆሳዕና፤ሰኔ 19/2016 (ኢዜአ)፦ የኦሎምፒክ ችቦ በተተኪ ስፖርተኞች ዘንድ መነሳሳት ለመፍጠር ከማገዝ ባለፈ የዜጎችን የእርስ በእርስ ግንኙነት ለማጎልበት ሚናው የጎላ መሆኑን የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ገለጸ።

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ "በፓሪስ 2024 ኦሎምፒክ ኢትዮጵያ ትወዳደር ተወዳድራም ታሸንፍ" በሚል መሪቃል የተዘጋጀ የኦሎምፒክ ችቦ ሽኝት መርሃ ግብር ዛሬ በሆሳዕና ከተማ ተካሂዷል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት በኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ የቦርድ አባል ዶክተር ጊዮን ሰይፉ እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያ በኦሎምፒክ ውድድር በርካታ ድሎችን በማስመዝገብ የምትታወቅ ሀገር ናት። 

ዘንድሮም በኦሎምፒክ ውድድር የሚመዘገበውን ውጤት ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

የኦሎምፒክ ችቦው በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች እየተዘዋወረ መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህም በተተኪ ስፖርተኞች ዘንድ መነሳሳትን ለመፍጠር ከማገዝ ባለፈ የዜጎችን አብሮነት ለማጎልበት ጉልህ ሚና አለው ብለዋል።


 

የክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዘሪሁን እሸቱ በበኩላቸው በክልሉ ለኦሎምፒክ ስፖርት ትኩረት መሰጠቱን ተናግረዋል።

የኦሎምፒክ ችቦ ወደክልሉ መምጣት በዘርፉ ዝንባሌ ያላቸውን ዜጎች ለመለየትና የዜጎችን አንድነት ለማጠናከር እድል መፍጠሩን ገልጸዋል።

ቢሮው ስፖርትን በማጠናከር በአካልና በስነ ልቦና የዳበረ ብቁ ዜጋ በብዛት ለማፍራት እየሰራ መሆኑንም አስረድተዋል። 


 

የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ዳዊት ጡምደዶ በበኩላቸው እንዳሉት በኦሎምፒክ ዘርፍ እየተመዘገበ ያለውን ውጤት አጠናክሮ ለማስቀጠል አስፈላጊው ድጋፍ ማድረግ ያስፈልጋል።

"የኦሎምፒክ ችቦ በከተማው በነበረው ቆይታ በዘርፉ ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት መነቃቃት ፈጥሯል" ያሉት አቶ ዳዊት፣ አስተዳደሩ ለስፖርት ዘርፍ ዝንባሌ ያላቸውን ወጣቶች እንደሚደግፍ አረጋግጠዋል።

ከተማዋ በተለያዩ የስፖርት ዘርፎች ብቁ ስፖርተኞች ያሉባት መሆኑንም ጠቁመዋል። 

ከሰኔ 8 ቀን ጀምሮ በክልሉ ቆይታ ያደረገው የኦሎምፒክ ችቦ ዛሬ ወደ ድሬዳዋ አስተዳደር ሽኝት ተደርጎለታል።

የሽኝት መርሃ ግብሩን በማስመልከትም ማስ ስፖርት እንዲሁም የሴቶችና የወንዶች የሦስት ሺህ ሜትር የሩጫ ውድድር ተካሂዷል።


 

ስፖርት በጥሩ ስነ ምግባር የታነጹ ዜጎችን ለማፍራት ሚናው የጎላ መሆኑን የተናገረው ደግሞ በ3 ሺህ ሜትር የሩጫ ውድድር ጉራጌ ዞንን ወክሎ የተሳተፈውና አሸናፊ የሆነው አትሌት በቀለ ተክሉ ነው።

የኦሎምፒክ ችቦ ሽኝት መርሃ ግብርን በማስመልከት በተዘጋጀ የሩጫ ውድድር አሸናፊ ለሆኑ አትሌቶች የገንዘብና የሜዳሊያ ሽልማት ተበርክቷል።

የ2024 የፓሪስ ኦሎምፒክ ውድድር ከሐምሌ 19 ቀን 2016 ጀምሮ የሚካሄድ ሲሆን በውድድሩም እንደሀገር የላቀ ውጤት ለማስመዝገብ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ታውቋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም