ኢትዮጵያና ኖርዌይ በአየር ንብረት ለውጥና በግብርናው መስክ ያላቸውን ትብብር የሚያጠናክር ምክክር አካሄዱ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያና ኖርዌይ በአየር ንብረት ለውጥና በግብርናው መስክ ያላቸውን ትብብር የሚያጠናክር ምክክር አካሄዱ
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 19/2016 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያና ኖርዌይ በአየር ንብረት ለውጥና በግብርናው መስክ ያላቸውን ትብብር የሚያጠናክር ምክክር ማካሄዳቸው ተገለጸ።
በግብርና ሚንስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) የተመራ የኢትዮጵያ ልዑክ በኖርዌይ ኦስሎ እየተካሄደ በሚገኘው የ”Oslo Tropical Forest Form” ላይ እየተሳተፈ ይገኛል።
የልዑክ ቡድኑ ከጉባኤው ጎን ለጎን የሁለትዮሽ ውይይት ከኖርዌይ የአየር ንብረት እና የአካባቢ ጥበቃ ሚኒስትር፣ ከኖርዌይ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣ ከኖርዌይ አለም አቀፍ የልማት ትብብር ኤጄንሲ (NORAD) ዋና ዳይሬክተር እንዲሁም ከኖርዌይ አለም አቀፍ አየር ንብረት እና ደን ኢንሼቲቭ (NICFI) ምክትል ዋና ዳይሬክተር ጋር ውጤታማ ውይይት አድርጓል፡፡
ኢትዮጵያ የቀጣናው ሀገራትን ጭምር ተጠቃሚ ያደረገ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ባለፉት ዓመታት በውጤታማነት መተግበሯን ልዑኩ በጎንዮሽ ውይይቱ አውስቷል።
ልዑኩ የኢትዮጵያ መንግስት ለአረንጓዴ አሻራና ለተራቆቱ መሬቶች ማገገሚያ ስላጸደቀዉ የልዩ ፈንድ አዋጅ ገለጻ አድረጎ፣ በበጋ ስንዴ፣ በሌማት ትሩፋት መርሐግብር እንዲሁም በስርዓተ ምግብ ትግበራ የመንግስትን የላቀ ቁርጠኝነት አመልክቷል።
ጤናው የተጠበቀ ማህበረሰብን በመገንባት ሂደት ከምርት ማምረት እስከ አጠቃቀም ሊኖር የሚገባ ስርዓተ ምግብ (Food System)ን በተመለከተ ኢትዮጵያ በትኩረት እየሰራች መሆኑም ተመልክቷል።
ኢትዮጵያ የግብርና ምርታማነትን በማሳደግና የተፈጥሮ ሀብትን በዘላቂነት በመጠበቅ ረገድ ያከናወነቻቸው ጉልህ ተግባራት በመልካም ተሞከሮነት በጉባኤው ቀርቦ አድናቆት ተችሮታል፡፡
በሁለትዮሽ ውይይቱ በኖርዌይ በኩል የተሳተፉ ባለስልጣናት ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ እያስከተለ ያለውን ተጽዕኖ ለመቋቋም እያከናወነች ያለውን ተግባር ማድነቃቸውን የግብርና ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።
የለውጥ ተግባሩ የሙቀት አማቂ ጋዝ ለመቀነስና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ብሎም የዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳካት የሚኖረውን ትልቅ ፋይዳ አውስተው የሀገራቱ ትብብር የበለጠ እንዲጠናከር እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል፡፡