በሕክምና ግብዓት ማምረት ላይ ለተሰማሩ አምራቾች የተሰጠው ትኩረት ምርታማነት እንዲጨምር የሚያደርግ ነው-አምራቾች - ኢዜአ አማርኛ
በሕክምና ግብዓት ማምረት ላይ ለተሰማሩ አምራቾች የተሰጠው ትኩረት ምርታማነት እንዲጨምር የሚያደርግ ነው-አምራቾች
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 19/2016(ኢዜአ)፦መንግሥት በሕክምና ግብዓት ምርት ለተሰማሩ አነስተኛና መካከለኛ አምራቾች የሰጠው ትኩረት ምርታማነት እንዲጨምር የሚያደርግ መሆኑን በዘርፉ የተሰማሩ አምራቾች ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) "ጤናችን በምርታችን" የሀገር ውስጥ የሕክምና ግብዓት የምርት እና ኢኖቬሽን ኤግዚቢሽንን ሰኔ 15 ቀን 2016 ዓ.ም በይፋ መክፈታቸው ይታወቃል።
በኤግዚቢሽኑ ላይ እንደተገለጸው በኢትዮጵያ አሁን ላይ 36 በመቶውን የመድኃኒትና የሕክምና ግብዓት በሀገር ውስጥ ምርት መሸፈን መቻሉ ተጠቅሷል።
በተያዘው በጀት ዓመትም የኢትዮጵያን የሕክምና ግብዓት ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ለተኪ ምርት ልማት በተሰጠ ትኩረት ከ50 ሚሊየን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ወጪን ማዳን መቻሉም እንዲሁ።
የሀገር ውስጥ አምራቾች እንዲበረታቱና አዳዲስ ኢንቨስተሮች በዘርፉ እንዲሰማሩ መደረጉ ለስኬቱ ቁልፍ ክንውኖች መሆናቸውን የጤና ሚኒስትሯ በቅርቡ መናገራቸው ይታወሳል።
የኢትዮጵያ የቆዳ መጠበቂያ እና የመድኃኒት አምራቾች ማኅበር ፕሬዝዳንት ሀሺም መሀመድ፤ መንግሥት ለአነስተኛና መካከለኛ አምራቾች የሰጠው ትኩረት የዘርፉን ተዋንያን የሚያበረታታ መሆኑን ገልፀዋል።
ለአብነትም የመድኃኒት ግዥ ለሀገር ውስጥ መድኃኒት አምራቾች መሰጠቱና በውጭ ምንዛሬ እንዲደገፉ የተደረገበት ሂደት ዋናው መሆኑን ገልፀዋል።
እንዲሁም በኤግዚቢሽኑ መክፈቻ ላይ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እነዚህ አምራቾች በሼድ እንዲሰሩ የተቀመጠው አቅጣጫ ትልቁን ችግር የሚፈታ መሆኑን አመላክተዋል።
የይልማና አነስተኛ የመድኃኒት ማምረቻ ምክትል ሥራ አስኪያጅ መስፍን መኮንን በበኩላቸው፤ መንግሥት ዘርፉን ለማጠናከር የሰጠው ትኩረት እንዲሁም አቅማቸውን ለማሳደግ እያከናወነ ያለው ሥራ የሚበረታታ መሆኑን ገልፀዋል።
ኤግዚቢሽኑ ከውጭ የሚገቡ መድኃኒቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት ዕቅድ መያዙን የሚያሳይ መሆኑን ተናግረዋል።
የቨርጂኒያ ፋርማሲቲካልስ ሽያጭ ባለሙያ ፋኑኤል አፈወርቅ ኤግዚቢሽኑ በሀገር ውስጥ የሚመረቱ ምርቶችን ለኅብረተሰቡ ለማስተዋወቅ ትልቅ ዕድል መፍጠሩን ተናግረዋል።
ለአነስተኛና መካከለኛ አምራቾች የውጭ ምንዛሬን በማስቀረት በኩልም ከፍተኛ አስተዋጽዖ እያበረከተ መሆኑን ገልፀዋል።
ሌላኛው አስተያየት ሰጪ የዩኒክ ኬሚካል ኢንዱስትሪ ባለቤት ጃፋር አህመድ፤ ኤግዚቢሽኑ ትልቅ ልምድ ያገኙበት መሆኑን ተናግረዋል።
በጥሬ እቃ አቅርቦት እንዲሁም ሙያዊ ሥልጠና በመስጠት እየተሰጣቸው ያለው ድጋፍ በምርታማነታቸው ላይ አዎንታዊ አስተዋጽዖ እያበረከተ መሆኑን ገልፀዋል።
ኤግዚቢሽኑ አነስተኛ የመድኃኒት አምራቾች ያለባቸውን ችግሮች ለማስረዳት ዕድል መፍጠሩን የገለፁት ደግሞ ከዩኒቨርስ ፋርማ ኢንዱስትሪ እና ትሬዲንግ የመጡት ቴዎድሮስ ጸጋዬ ናቸው።
አስተያየት ሰጪዎቹ የውጭ ምንዛሬና ካፒታል ዘርፉን የሚፈትኑ መሆናቸውን ገልጸው፤ ለዚህም ድጋፍ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል።
"ጤናችን በምርታችን" በሚል መሪ ኃሳብ የተከፈተው ኤግዚቢሽን ከ110 በላይ የዘርፉ አምራቾች የተሳተፉ ሲሆን፤ ከሰኔ 15 እስከ 20 ቀን 2016 ዓ.ም ለጉብኝት ክፍት ሆኖ መቆየቱ ይታወቃል።
በዚህ ኤግዚቢሽን በኢትዮጵያ የሕክምና ኢንቨስትመንት ዕድሎችን እንዲሁም የሀገር ውስጥ የሕክምና ምርትና አገልግሎቶች ለዕይታ ቀርበዋል።