ቀጥታ፡

ባለፉት 11 ወራት ለውጭ ገበያ የቀረበ የቅመማቅመም ምርት 7 ነጥብ 5 ሚሊየን ዶላር ገቢ ተገኘ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 19/2016(ኢዜአ) ባለፉት 11 ወራት ለውጭ ገበያ ከቀረበ  ቅመማቅመም ምርት 7 ነጥብ 5 ሚሊየን ዶላር ገቢ መገኘቱን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን አስታወቀ፡፡

ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ከቡና በተጨማሪ ቅመማቅመምና ሻይ ምርት ላይ ከልማት እስከ ግብይት የእሴት ሰንሰለቱን ተከትሎ ምርት የመጨመር፣ ጥራት የመጠበቅና ገበያ የማፈላለግ ብሎም የውጭ ምንዛሬ ግኝት ማሳደግ ላይ በትኩረት ይሰራል።

የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፤ በኢትዮጵያ ከ50 በላይ ቅመማቅመሞች የሚመረቱ ሲሆን፤ ከእነዚህም ውስጥ 16 የቅመማቅመም ዓይነቶች ለዓለም ገበያ ይቀርባሉ፡፡

በዋነኝነት ኮረሪማ፣ ዕርድ፣ ጥምዝ፣ ቁንዶ በርበሬ እና በርበሬ ያሉ ቅመሞች በዚህ ረገድ ተጠቃሽ ናቸው፡፡

ምርቶችም ወደ 39 የተለያዩ አገራት እንደሚላኩም ነው የጠቀሱት፡፡


 

በበጀት ዓመቱ 11 ወራት 8 ሺህ 400 ቶን ቅመማቅመም ወደ ተለያዩ የዓለም አገራት በመላክ 7 ነጥብ 5 ሚሊየን ዶላር መገኘቱንም ነው ያነሱት፡፡

አፈጻጸሙ  ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር በመጠን ሲነጻጸር ከ2 ሺህ ቶን በላይ ብልጫ ማሳየቱንም ተናግረዋል፡፡

የቅመማቅመም ደረጃ አወጣጥ ሥርዓቱ አለመዘመን እንዲሁም በተቋም ደረጃ ላቦራቶሪዎች አለመኖራቸው ኢትዮጵያ በዘርፉ ባላት አቅም ልክ እንዳትጠቀም ማነቆ መፍጠሩንም አንስተዋል፡፡

የቅመማቅመም ምርት ካሁን በፊት ስትራቴጂ እንዳልነበረው ጠቅሰው፤ በቀጣይ እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ ስትራቴጂ ተነድፎ እየተሰራ ነው ብለዋል።

በሚቀጥለው ዓመት ከዘርፉ የተሻለ ገቢ ለማግኘት የጥራትና ምዘና አክሪዲቴሽን ላቦራቶሪ ሥርዓት እንዲኖር ከንግድ ሚኒስቴር ጋር በቅርበት እየተሰራ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡

ባለኃብቶች በቅመማቅመም ምርት ዘርፍ በስፋት እንዲሰማሩም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም