ቀጥታ፡

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በዘንድሮው ክረምት 70 ሚሊየን ችግኞችን  ለመትከል ዝግጅት ተደርጓል

አዲስ አበባ ፤ሰኔ 19/2016 (ኢዜአ)፦ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር 70 ሚሊየን  ችግኞችን  ለመትከል  ዝግጅት  መደረጉን  የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር  አሻድሊ ሀሰን ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት  ሰኔ 14 ቀን 2016 ዓ.ም “ የምትተክል አገር የሚያፀና ትውልድ!" በሚል ሀሳብ የዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ ማስጀመሪያ መርሃ-ግብር በቅርቡ መካሄዱ ይታወቃል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ በሚካሄደው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር 7 ነጥብ 5 ቢሊየን ችግኞች በመትከል በአረንጓዴ አሻራ የተተከሉ ችግኞችን ቁጥር ወደ 40 ቢሊየን ከፍ  ለማድረግ መሆኑን  ተናግረው ነበር ፡፡

ባለፉት  አምስት ዓመታት በተካሄደው የአረንጓዴ  አሻራ መርሃ-ግብር የኢትዮጵያ የደን ሽፋን በ2011ዓ. ም. ከነበረበት 17 ነጥብ 2 በመቶ ወደ 23 ነጥብ 6 በመቶ ከፍ ማድረግ  መቻሉም ተገልጿል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል  ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን ለኢዜአ  እንደገለጹት፤  የሀገር አቀፍ የአረንጓዴ  አሻራ መርሃ-ግብር  የታለመለትን  ዓላማ እንዲያሳካ ክልሉ ትኩረት  ሰጥቶ እየሰራ ነው።

በዚህም በተያዘው ክረምት ችግኞችንና የመትከያ ጉድጓዶችን  የማዘጋጀት  ሥራዎች  መከናወናቸውን   ተናግረዋል።   


 

በመሆኑም በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር 70 ሚሊየን ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት   መጠናቀቁን  ጠቁመው፤ በአንድ ጀንበር ብቻ 15 ሚሊየን   ችግኞች  ለመትከል ዝግጅት መጠናቀቁን አስረድተዋል።

በአረንጓዴ አሻራ  መርሃ-ግብሩ እየተተከሉና ለተከላ የተዘጋጁ  ችግኞች አብዛኛዎቹ  ለምግብነት  የሚውሉ አትክልትና ፍራፍሬዎች  መሆናቸውን አብራርተዋል።

ይህም በክልሉ እየተከናወነ ያለውን የምግብ ዋስትናን  ለማረጋገጥ  የሚደረገውን ጥረት እንደሚያግዝ  ተናግረዋል። 

በክልሉ በባለፈው ዓመት የአረንጓዴ አሻራ  መርሃ-ግብር ከ55 ሚሊየን በላይ ችግኞች መተከላቸውን የክልሉ ግብርና  ቢሮ መረጃ ያመለክታል፡፡

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም