የሀረሪ ክልል ዳኞች አስተዳደር ጉባኤ ጥፋተኛ ሆነው የተገኙ የፍርድ ቤት ዳኞች እና የጉባኤ ተሿሚዎች ላይ የስራ ስንብት እና የደሞዝ ቅጣት ውሳኔ አስተላለፈ - ኢዜአ አማርኛ
የሀረሪ ክልል ዳኞች አስተዳደር ጉባኤ ጥፋተኛ ሆነው የተገኙ የፍርድ ቤት ዳኞች እና የጉባኤ ተሿሚዎች ላይ የስራ ስንብት እና የደሞዝ ቅጣት ውሳኔ አስተላለፈ
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 18/2016(ኢዜአ)፦የሀረሪ ክልል ዳኞች አስተዳደር ጉባኤ ጥፋተኛ ሆነው የተገኙ የፍርድ ቤት ዳኞች እና የጉባኤ ተሿሚዎች ላይ የስራ ስንብት እና የደሞዝ ቅጣት ዉሳኔ ማስተላለፉ ተገለጸ።
የክልሉ ዳኞች አስተዳደር ጉባኤ የዲሲፕሊን ክስ በተመሰረተባቸው የፍርድ ቤቱ ዳኞች እና የጉባኤ ተሿሚዎች ላይ የስራ ስንብት እና የደሞዝ ቅጣት ውሳኔ አስተላልፋል።
ጉባኤው ባለፉት ወራት ከተገልጋዩ ማህበረሰብ የቀረቡ ቅሬታዎችን እንዲሁም የኢኒስፔክሽን ባለሙያዎች ያደረጉትን ማጣራትና የምርመራ ውጤቶች መነሻ በማድረግ የፍርድ ቤቱ ዳኞች ስነ-ምግባር ደንብን በመተላለፍ የዲሲፕሊን ጥፋት በፈፀሙ ዳኞችና የጉባኤ ተሿሚዎች ላይ ክስ ተመስርቶ ለክልሉ ዳኞች አስተዳደር ጉባኤ የቀረበ መሆኑን አስታውሷል።
ጉባኤውም የቀረበለትን የዲሲፕሊን ክስና ማስረጃዎች ከህጉ አንፃር አገናዝቦ በመመርመር ከቀረበለት 13 ክሶች መካከል 10 ክሶች ላይ ጥፋት መፈፀሙን በማረጋገጥ ክስ የቀረበባቸው 5 ዳኞች እና 4 የጉባኤ ተሿሚዎች ጥፋተኛ ናቸው ሲል ውሳኔ ሰጥቷል።
በዚሁ መሠረት ጥፋተኛ የተባሉ 1 የሸሪአ ፍርድ ቤት ዳኛ እና 2 የጉባኤ ተሿሚ ባለሙያዎች ከስራ እንዲሰናበቱ የተወሰነ ሲሆን፣ 1 የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ፣ 2 የከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኞች እና 1 የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ዳኛ በአራት ወር ደሞዝ እንዲቀጡ፣ 1 የተከላካይ ጠበቆች አስተባባሪ ከደሞዝና ደረጃ ዝቅ እንዲል፣ 1 የጉዳዮች ፍሰት አስተዳደር ባለሙያ የሶስት ወር ደሞዝ እንዲቀጡ ጉባኤው የቅጣት ውሳኔ አስተላልፏል።
የተለያዩ ውስንነቶች የነበሩባቸው 2 ዳኞች ያቀረቡት የስራ መልቀቂያ ጥያቄ ተቀባይነት አግኝቶ ከስራ እንዲሰናበቱ ውሳኔ ሰጥቷል።
ከዚህ ጋር ተያይዞ የክልሉ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንቶች ማኔጅመንት ባከናወነው ግምገማ ክፍተት አለባቸው ተብለው በተለዩ መደቦች ላይ ለዳኞች እና ለጉባኤ ተሿሚዎች የስራ ድልድል ማከናወኑ ተመላክቷል።
በዚሁ መሠረት በቀረበባቸው የዲሲፕሊን ክስ ጥፋተኛ ተብለው የቅጣት ውሳኔ የተላለፈባቸዉ 3 ዳኞች ከዳኝነት/ከችሎት/ ስራ ተነስተው በሌሎች የአስተዳደር ስራዎች ላይ እንዲመደቡ የተደረገ መሆኑንና 1 የተከላካይ ጠበቆች አስተባባሪ ከአስተባባሪነት ተነስተው በባለሙያነት እንዲሰሩ ዉሳኔ ማስተላለፉ ተገልጿል።
በቀጣይም የተጠያቂነት ስርዓትን በማጠናከር ከመሠረታዊ የብቃት ማነስ እና ከስነ-ምግባር ብልሹነት ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ ችግሮችን ህግና ስርዓትን ተከትሎ እንዲቀረፉ በማድረግ የማጥራቱን ስራ ሙሉ በሙሉ ለመተግበር ጉባኤው በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ተገልጿል።
በሀረሪ ክልል ፍርድ ቤቶች ከአገልግሎት አሰጣጥ እንዲሁም ከስነ-ምግባር ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመቅረፍ ቀልጣፋ እና ጥራት ያለው አገልግሎት በመስጠት የተገልጋይ እርካታና ታዕማኒነትን ማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራት ለማከናወን የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት እቅድ ይዞ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት አስታውቋል።
በተያዘው እቅድ የዳኝነት ነፃነት የማረጋገጥ ተግባር እንደተጠበቀ ሆኖ የተጠያቂነት ስርዓትን የማጠናከር ስራ ትኩረት ተሰጥቶት ተገልጋዩ ማህበረሰብ በየደረጃው ቅሬታ የሚያቀርብበትን አደረጃጀት ከመፍጠር ባለፈ የሚቀርቡ ቅሬታዎች በአጭር ጊዜ ምላሽ እንዲያገኙ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑ ተጠቁሟል።
ከዚህም ባለፈ በዳኞች አስተዳደር ጉባኤ ጽህፈት ቤት ስር የኢኒስፔክሽን ክፍልን በዳይሬክቶሬት ደረጃ በማዋቀር ከሚቀርቡ ቅሬታዎች በተጨማሪ በሁሉም ደረጃ የሚገኙ የፍርድ ቤቱ ዳኞችን መዝገቦች ድህረ ምርመራ ስራ/ሌጋል ኦዲት/ እየተከናወነ እንደሚገኝ የክልሉ ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት መረጃ ያመለክታል።