ቀጥታ፡

የባንክ ስራ ረቂቅ አዋጅ ዘርፉን በማዘመን ዓለም አቀፍ ትስስርና ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ ያለመ ነው-የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጂጌ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 18/2016(ኢዜአ)፦ የባንክ ስራ ረቂቅ አዋጅ ዘርፉን በማዘመን ዓለም አቀፍ ትስስርና ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ ያለመ  መሆኑን  በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጂጌ ገለጹ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 34ኛ መደበኛ ስብሰባውን አካሂዷል።


 

ምክር ቤቱ በስብሰባው ከተወያየባቸው አጀንዳዎች መካከል የባንክ ሥራ ረቂቅ አዋጅን መርምሮ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ መምራት ይገኝበታል።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ የአዋጁን አስፈላጊነት እና የአዋጁን የውሳኔ ሀሳብ ለምክር ቤቱ አቅርበዋል።

የባንክ ዘርፉ ከዓለም ገበያ ጋር ያለውን ትስስር ለማጠናከር፣ በዘመናዊ ቴክኖሎጂና እውቀት እንዲደገፍ በማድረግ ተወዳዳሪነትን ለማስፋት፣ በቂ የፋይናንስ አቅርቦት እንዲኖር እንዲሁም የሥራ እድል ፈጠራን ማሳለጥ የረቂቅ አዋጁ ዓላማ ነው ብለዋል።

የውጭ አገር ዜግነት ያላቸው ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በባንክ አገልግሎት ዘርፍ እንዲሰማሩ የሚያስችል የፖሊሲ ማሻሻያ መደረጉን የመንግስት ዋና ተጠሪው አስታውሰዋል።

ረቂቅ አዋጁም ባንኮች የዲጂታል ዘዴዎችን በመጠቀም የፋይናንስ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት እንዲሆኑ የሚያስችል መሆኑን ጠቅሰዋል።

አዋጁ ሙሉ በሙሉ ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት የሚሰጡ ባንኮችም እንዱስትሪውን እንዲቀላቀሉ የሚፈቅድ መሆኑንም አስረድተዋል።

የምክር ቤቱ አባላት በበኩላቸው በሰጡት አስተያየት ዘርፉን ክፍት ለማደረግ እየተደረጉ ያሉ እንቅስቃሴዎች መልካም የሚባሉ መሆናቸውን አንስተዋል።

እንዲያም ሆኖ የአገር ውስጥ ባንኮች ከውድድር ውጪ እንዳይሆኑ ምን ዓይነት የተዘረጋ አሰራር አለ?፣ በቴክኖሎጂ፣ በኃብት እና በሰው ኃይል በቂ ዝግጅት አድርገዋል ወይ? የሚለው ጉዳይ ሊጤን እንደሚገባው አጽንዖት ሰጥተዋል።

ባንኮችን በተገቢው መንገድ ቁጥጥር ማደረግ የሚቻልባቸው ሁኔታዎች በአዋጁ በጥልቀት መመላከት እንዳለባቸውም ነው አስተያየታቸውን የሰጡት።

ምክር ቤቱ በባንክ ሥራ ረቂቅ አዋጁ ላይ ከተወያየ በኋላ ለፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ለዝርዝር ዕይታ በሙሉ ድምጽ መርቷል።

 


 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም