ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በ"ፉትሳል" እግር ኳስ ፕሮጀክት ሥልጠና ተጀመረ

ደብረ ብርሃን ፤ ሰኔ 18/2016(ኢዜአ)፦  በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በ"ፉትሳል" እግር ኳስ  ፕሮጀክት ሥልጠና ዛሬ በደብረ ብርሃን መሰጠት ጀምሯል። 

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽን 'አክሰዴ'  ከተባለ ግብረ ሰናይ ድርጅት ጋር በመተባበር በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በ"ፉትሳል" እግር ኳስ  ፕሮጀክት ሥልጠና ዛሬ በደብረ ብርሃን መስጠት ጀምሯል።

የ''ፉትሳል'' ስፖርት በ 4 ተጫዋች እና በ 1 በረኛ የሚደረግ ሲሆን በአጠቃላይ በ5 የአንድ ቡድን አባላት የሚደረግ ጨዋታ ሆኖ  ሙሉ ጫወታው 40 ደቂቃ ክፍለ ጊዜ አለው።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ በስልጠናው ማስጀመሪያ እንዳሉት የኢትየጵያን እግር ኳስ  ስፖርት በማሳደግ ለገፅታ ግንባታና ለኢኮኖሚያዊ እድገት መጠቀም ይገባል።


 

በዚህም ታዳጊ ስፖርተኞች ላይ መሰረት ያደረገ የቴክኒክ፣ የአካል ብቃትና የእግር ኳስ ክህሎትን በዘመናዊ መልኩ ማሳደግ ይገባል ብለዋል።

ለዚህም የአስተዳደር አካላት፣ ባለሃብቶችና ኩባንያዎችን በማሳተፍ ክለቦች ላይ የተመሰረተ ሥልጠና መስጠት ድጋፍ  እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

በተለይም ባለሀብቶች ስፖርቱን ለኢንቨስትመንትና ለሥራ ዕድል ፈጠራ በማዋል ሚና እንዲጫወቱ ፕሬዚዳንቱ ጠይቀዋል።

የደብረ ብርሃን ስፖርት ክለብ በአገሪቱ የመጀመሪያ የሆነውን የ'ፉትሳል' እግር ኳስ ስልጠና ለመስጠት ያደረገው እንቅስቃሴ የሚያበረታታ መሆኑን ገልጸው፣ ፌደሬሽኑም ስፖርቱን ለማስፋፋት ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል። 

ስልጠናው ወጣት ስፖርተኞችን ለማፍራትና ስፖርቱን ለማስፋፋት እገዛ እንደሚያደርግ ፕሬዚዳንቱ እምነታቸውን ገልጸዋል። 

ሥልጠናው በተባባሪነት የሚሰጠው 'አክሰዴ' ድርጅት ተወካይ አቶ ይመር ሃይሌ ድርጅታቸው በኢትዮጵያ እግር ኳስን ለማስፋፋትና ብቁ ተጫዋቾች ለማፍራት በሚደረገው ጥረት ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።

የ'ፉትሳል' ስፖርት የታዳጊ ወጣቶችን  የርስ በርስ ግንኙነት ከማሳደግ ባለፈ፤ የስፖርት ማርኬቲንግን ለማስፋፋት እንደሚረዳም አስረድተዋል።

ለዚህም በስፖርት ትጥቅ አቅርቦት፣ የአሰልጣኞች ስልጠና በመስጠትና ተያያዥነት ባላቸው መስኮች ድጋፍ በማድረግ ስፖርቱ ወደ ሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች ለማስፋፋት ዕቅድ እንዳለው ተናግረዋል።

የደብረ ብርሃን እግር ኳስ ክለብ ዋና አሰልጣኝ አቶ ሰለሞን አየለ፣ ፕሮጀክቱ ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ ስፖርት ውድድሮች ተሳትፎዋን የምታጠናክርበት መልካም አጋጣሚ የሚፈጥር ነው ብለዋል።

ለሁለት ዓመታት በሚዘልቀው ሥልጠና በስምንት ፕሮጀክቶች የታቀፉ 120  ታዳጊ ወጣቶች እንደሚሳተፉበት ተናግረዋል። 

ሥልጠናው የወጣቶቹን የትምህርትና የዕረፍት ጊዜ ባገናዘበ መልኩ እንደሚሰጥ አቶ ሰለሞን አስረድተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም