የኮሪደር እና የወንዝ ዳርቻ ልማት ሥራዎች የአካባቢ ብክለትን ለመግታት እየተከናወኑ ላሉ ተግባራት ተጨማሪ አቅም የሚፈጥሩ ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
የኮሪደር እና የወንዝ ዳርቻ ልማት ሥራዎች የአካባቢ ብክለትን ለመግታት እየተከናወኑ ላሉ ተግባራት ተጨማሪ አቅም የሚፈጥሩ ናቸው
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 18/2016(ኢዜአ)፦የኮሪደር እና የወንዝ ዳርቻ ልማት ሥራዎች የአካባቢ ብክለትን ለመግታት እየተከናወኑ ላሉ ተግባራት ተጨማሪ አቅም የሚፈጥሩ መሆናቸውን የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን አስታወቀ።
የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን የአካባቢ ብክለት መግቻ ስልቶች ላይ ያተኮረ ሀገራዊ ሴሚናር ከባለድርሻ አካላት ጋር እያካሄደ ይገኛል።
በመድረኩም በፕላስቲክ፣ በአየር እና በውሃ ብክለቶች ዙሪያ ሰነዶች ቀርበው ዛሬን ጨምሮ ለሁለት ቀናት ውይይት ይደረጋል።
የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ፍሬነሽ መኩሪያ በዚሁ ወቅት፤ ባለፉት ወራት “ብክለት ይብቃ ውበት ይንቃ" በሚል መሪ ሃሳብ የስድስት ወር የአካባቢ የብክለት መግቻ ንቅናቄ እያካሄደ መሆኑን ተናግረዋል።
ከዚህም ጋር ተያይዞ በአገር አቀፍ ደረጃ ከ3 ነጥብ 6 ሚሊየን በላይ ሕዝብ የተሳተፈበት የፕላስቲክና የአየር ብክለት መግቻ ሃገር አቀፍ ንቅናቄ መካሄዱን ጠቅሰዋል።
የተለያዩ ሚዲያዎችን በመጠቀም ከ35 ሚሊየን በላይ ለሚሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች በፕላስቲክ ብክለት ዙሪያ ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ መከናወኑን አንስተዋል፡፡
በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች በማስተባበርም በመጤ ወራሪ አረም የተበከሉ ሃይቆችን የማጽዳት ሥራ መከናወኑን ተናግረዋል።
በተጨማሪም ውሃን የሚበክሉ ኬሚካሎችና ቆሻሻዎችን የሚያመነጩ አምራችና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ሳይንሳዊ መንገድን ተከትለው እንዲያስወግዱ ምክረ-ሀሳብ የመስጠት፣ የመከታተልና የመቆጣጠር እንዲሁም እርምት እርምጃዎችን የመውሰድ ሥራ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ መምጠቱን ተናግረዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና በሀገሪቱ ዋና ዋና ከተሞች እየተከናወኑ ያሉ የኮሪደር እና የወንዝ ዳርቻ ልማት ሥራዎች የአካባቢ ብክለትን ለመግታት እየተከናወኑ ላሉ ተግባራት ተጨማሪ አቅም የሚፈጥሩ መሆናቸውንም ነው ያነሱት፡፡
በመድረኩ በኢትዮጵያ የፕላስቲክ ምርቶችን በተመለከተ የውይይት መነሻ ጽሑፍ ያቀረቡት የሥርዓተ- ምኅዳር ፍትሕ ኢትዮጵያ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር እስከዳር አውግቸው፤ በኢትዮጵያ በፕላስቲክ ተረፈ ምርት ወይም ቆሻሻ ምክንያት የሚከሰት የአካባቢ ብክለት እየጨመረ መምጣቱን ተናግረዋል።
የፕላስቲክ ቆሻሻዎች በሰው እና በእንስሳት ጤና ላይ የሚያደርሱት ጉዳት ከፍተኛ መሆኑን አንስተው፤ መሰል ቆሻሻዎችን በአግባቡ ማስወገድ ይገባል ነው ያሉት፡፡
በኢትዮጵያ የፕላስቲክ ቆሻሻ አያያዝ ስትራቴጂ ዙሪያ ጽሑፍ ያቀረቡት የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ከፍተኛ የሕግ አማካሪ አየለ ሄጌና (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የፕላስቲክ ምርቶች በኢትዮጵያ እያስከተሉት ያለውን ጉዳት ለመከላከል ስትራቴጂ ተነድፎ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የፕላስቲክ ቆሻሻ አወጋገድን በተመለከተ ያለው ግንዛቤ ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻል እያሳየ መምጣቱንም አንስተዋል፡፡