ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ለ33 የመካከለኛው ምስራቅና የአፍሪካ አገራት የእንስሳት ክትባት እየላከች ነው

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 18/2016(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ በእንስሳት ክትባት መድኃኒት እራሷን ከመቻል ባለፈ ለ33 የመካከለኛው ምስራቅና የአፍሪካ አገራት በመላክ የውጭ ምንዛሬ ገቢ እያገኘች  መሆኑን ብሔራዊ የእንስሳት ጤና ጥበቃ ኢንስቲትዩት አስታወቀ። 

በብሔራዊ የእንስሳት ጤና ጥበቃ ኢንስቲትዩት የክትባት ሽያጭና ደንበኞች አገልግሎት ቡድን መሪ ደበበ ሺመክት፤ ኢንስቲትዩቱ 1956 ዓ.ም በቢሾፍቱ ከተማ እንደተመሠረተ አስታውሰዋል።

ባለፉት 60 ዓመታትም የእንስሳት በሽታ መከላከያ ክትባቶችን በማምረት ከሀገር ፍላጎት በተጨማሪ ለውጭ ሀገራት ገበያ በማቅረብ ላይ እንደሚገኝ ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ አርብቶና አርሶ አደሩን ማኅበረሰብ የቁም እንስሳት የሁለንተናዊ የኢኮኖሚ ምንጭ በመሆናቸው ኢንስቲትዩቱ የእንስሳት ኃብቶቻቸውን ጤንነት በመጠበቅ ከፍተኛ ሚና እየተወጣ እንደሚገኝ አንስተዋል።

ኢንስቲትዩቱ በባክቴሪያና በቫይረስ አማካኝነት በእንስሳት ላይ የሚከሰቱ በሽታዎችን  ቀድሞ መከላከል የሚያስችሉ መድኃኒቶችን በማምረት ለገበያ የማቅረብ ሥራ እየተሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

በዚህም ዶሮ፣ ግመል፣ ውሻ እና የዳልጋና የጋማ ከብቶችን ጨምሮ ለቤት እንስሳት የሚሰጡ 23 ዓይነት የቅድመ-በሽታ መከላከል  የክትባት መድኃኒቶችን በማምረት እያቀረበች መሆኑን ተናግረዋል። 

አገሪቱ ባለፉት 11 ወራት ብቻ 41 ነጥብ 5 ሚሊየን ዶዝ የእንስሳት ክትባት መድኃኒት ወደ ውጭ መላኳንና ለአገር ውስጥ፤ 292 ሚሊየን ዶዝ ማቅረቧን አብራርተዋል።



ኢንስቱትዩቱ የሀገር ውስጥ የእንስሳት ሕክምና መድኃኒት ፍጆታ ከማሟላት ባለፈ፤ በአጠቃላይ ለሦስት የመካከለኛው ምስራቅ አገራትና 30 የአፍሪካ አገራት የእንስሳት መድኃኒት እየላከች መሆኑን አስታውቀዋል።  

ቻድና ደቡብ ሱዳን እንዲሁም ሌሎች ከፍተኛ የቁም እንስሳት ቁጥር ያላቸው የአፍሪካ አገራት ሲሆኑ፤ ለእንስሳት ክትባት የሚውሉ መድኃኒቶችን ከኢትዮጵያ በመውሰድ እየተገለገሉ ይገኛል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ላለፉት በርካታ ዓመታት ለእንስሳት የሚያስፈልጋትን የክትባት መድኃኒት ከውጭ አገር አታስገባም ያሉት አቶ ደበበ፤ በዚህም የውጭ ምንዛሬ ማስቀረት ተችሏል ብለዋል።

ወደ መካከለኛው ምስራቅና የአፍሪካ አገራት የሚላከው የክትባት መድኃኒት የውጭ ምንዛሬ ገቢ በማስገኘት የአገርን ኢኮኖሚ እየደገፉ እንደሚገኝ ገልፀዋል።

ኢትዮጵያ ለእንስሳት ክትባት የሚያስፈልጋትን መድኃኒት ማምረት የሚችል ተቋም በመፍጠር ከአፍሪካ ቀዳሚ  መሆን እንደተቻለ ገልፀዋል።

በቀጣይም ውጤታማ የጥናትና ምርምር ሥራ በማከናወን በእንስሳት ላይ ሊከሰቱ የሚችሉ በሽታዎችን በመከላከል ኢትዮጵያ ጤንነቱ የተጠበቀ የእንስሳት ኃብት እንዲኖራት ለማስቻል በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ብሔራዊ የእንስሳት ጤና ጥበቃ ኢንስቲትዩት ከተመሠረተ 60 ዓመት ያስቆጠረ ሲሆን፤ አሁን ላይ  በዓመት 350 ሚሊየን ዶዝ ክትባት የማምረት አቅም ፈጥሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም